ትንቢተ ሶፎንያስ
1 ፤ በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን ወደ ሕዝቅያስ ልጅ ወደ አማርያ ልጅ ወደ ጎዶልያስ ልጅ ወደ ኵሲ ልጅ ወደ ሶፎንያስ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2 ፤ ነገርን ሁሉ ከምድር ፊት ፈጽሜ አጠፋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
3 ፤ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ የሰማይን ወፎችና የባሕርን ዓሣዎች ማሰናከያንም ከኃጢአተኞች ጋር አጠፋለሁ፤ ሰውንም ከምድር ፊት እቈርጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
4 ፤ እጄንም በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እዘረጋለሁ፤ ከዚህም ስፍራ የበኣልን ቅሬታና የጣዖታቱን ካህናት ስም አጠፋለሁ፤
5 ፤ በሰገነትም ላይ ለሰማይ ሠራዊት የሚሰግዱትን፥ በእግዚአብሔርና በንጉሣቸው በሚልኮም ምለው የሚሰግዱትን፥
6 ፤ እግዚአብሔርንም ከመከተል የተመለሱትን፥ እግዚአብሔርንም ያልፈለጉትንና ያልጠየቁትን አጠፋለሁ።
7 ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፥ እግዚአብሔር መሥዋዕትን አዘጋጅቶአልና፥ የጠራቸውንም ቀድሶአልና በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ።
8 ፤ በእግዚአብሔርም መሥዋዕት ቀን አለቆችንና የንጉሥን ልጆች እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እቀጣለሁ።
9 ፤ በዚያም ቀን በመድረኩ ላይ የሚዘልሉትን፥ የጌታቸውን ቤት ዓመፃንና ሽንገላን የሚሞሉትን እቀጣለሁ።
10 ፤ በዚያ ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ከዓሣው በር የጩኸት ድምፅ፥ ከከተማውም በሁለተኛው ክፍል ውካታ፥ ከኮረብቶቹም ታላቅ ሽብር ይሆናል።
11 ፤ እናንተ በመክቴሽ የምኖሩ ሆይ፥ የከነዓን ሕዝብ ሁሉ ጠፍተዋልና፥ ብርም የተሸከሙ ሁሉ ተቈርጠዋልና አልቅሱ።
12 ፤ በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን በመብራት እመረምራለሁ፤ በአተላቸውም ላይ የሚቀመጡትን፥ በልባቸውም። እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፥ ክፉም አያደርግም የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ።
13 ፤ ብልጥግናቸውም ለምርኮ ይሆናል፥ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፤ ቤቶችንም ይሠራሉ፥ ነገር ግን አይቀመጡባቸውም፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁን ግን አይጠጡም።
14 ፤ ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል፤ ኃያሉም በዚያ በመራራ ልቅሶ ይጮኻል።
15 ፤ ያ ቀን የመዓት ቀን የመከራና የጭንቀት ቀን፥ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፥ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፥
16 ፤ በተመሸጉ ከተሞችና በረዘሙ ግንቦች ላይ የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን ነው።
17 ፤ በእግዚአብሔርም ላይ ኃጢአት ሠርተዋልና እንደ ዕውር እስኪሄዱ ድረስ ሰዎችን አስጨንቃለሁ፤ ደማቸውም እንደ ትቢያ፥ ሥጋቸውም እንደ ጕድፍ ይፈስሳል።
18 ፤ በእግዚአብሔርም ቍጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ እርሱም በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥኖ ይጨርሳቸዋልና ምድር ሁሉ በቅንዓቱ እሳት ትበላለች።