መጽሐፈ ሳሙኤል ካል. Chapter 14

1 ፤ የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ ወደ አቤሴሎም እንዳዘነበለ አወቀ።
2 ፤ ኢዮአብም ወደ ቴቁሔ ልኮ ከዚያ ብልሃተኛ ሴት አስመጣና። አልቅሺ፥ የኀዘንም ልብስ ልበሺ፥ ዘይትም አትቀቢ፥ ስለ ሞተ ሰውም ብዙ ዘመን እንደምታለቅሺ ሁኚ፤
3 ፤ ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ ያለውን ቃል ንገሪው አላት፤ ኢዮአብም ቃሉን በእርስዋ አፍ አደረገ።
4 ፤ እንዲሁም የቴቁሔይቱ ሴት ወደ ንጉሥ ገብታ በግምባርዋ በምድር ላይ ወደቀች፥ እጅ ነሥታም። ንጉሥ ሆይ፥ አድነኝ አለች።
5 ፤ ንጉሡም። ምን ሆነሻል? አላት። እርስዋም መልሳ አለች። በእውነት እኔ ባሌ የሞተብኝ ባልቴት ሴት ነኝ።
6 ፤ ለእኔም ለባሪያህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፥ በሜዳም ተጣሉ፤ የሚገላግላቸውም አልነበረም፥ አንዱም ሌላውን መትቶ ገደለው።
7 ፤ እነሆም፥ ዘመዶች ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሥተው። ስለ ገደለው ስለ ወንድሙ ነፍስ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን አውጪ አሉኝ፤ እንዲሁም ደግሞ ወራሹን የቀረውን መብራቴን ያጠፋሉ፥ የባሌን ስምና ዘርም ከምድር ላይ አያስቀሩም።
8 ፤ ንጉሡም ሴቲቱን። ወደ ቤትሽ ሂጂ፥ እኔም ስለ አንቺ አዝዛለሁ አላት።
9 ፤ የቴቁሔይቱም ሴት ንጉሡን። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ኃጢአቱ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሕ ይሁን አለችው።
10 ፤ ንጉሡም። የሚናገርሽን አምጪልኝ፥ ከዚያም በኋላ ደግሞ አይነካሽም አለ።
11 ፤ እርስዋም። ደም ተበቃዮችም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳያጠፉ ልጄንም እንዳይገድሉ፥ ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን ያስብ አለች። እርሱም። ሕያው እግዚአብሔርን! ከልጅሽ አንድ ጠጕር በምድር ላይ አይወድቅም አለ።
12 ፤ ሴቲቱም። እኔ ባሪያህ ለጌታዬ ለንጉሥ አንድ ቃል ልናገር አለች፤ እርሱም። ተናገሪ አለ።
13 ፤ ሴቲቱም አለች። በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ስለ ምን አሰብህ? ንጉሡ ይህን ነገር ተናግሮአልና ያሳደደውን ስላላስመለሰ በደለኛ ነው።
14 ፤ ሁላችን እንሞታለን፥ በምድርም ላይ እንደ ፈሰሰና እንደማይመለስ ውኃ ነን፤ እግዚአብሔርም የነፍስን ጥፋት አይወድድም፥ ነገር ግን የተጣለ ሰው ፈጽሞ እንዳይጠፋ በምክሩ ያስባል።
15 ፤ አሁንም ሕዝቡ ስለሚያስፈራኝ ይህን ነገር ለጌታዬ ለንጉሥ እነግረው ዘንድ መጥቻለሁ፤ እኔም ባሪያህ። ምናልባት የእኔን የባሪያውን ልመና ንጉሡ ያደርግልኝ እንደሆነ ለንጉሡ ልናገር፤
16 ፤ እርስዋንና ልጅዋን ከእግዚአብሔር ርስት ያጠፋቸው ዘንድ ከሚሻ ሰው እጅ ያድን ዘንድ ንጉሡ ባሪያውን ይሰማል አልሁ።
17 ፤ እኔም ባሪያህ። መልካሙንና ክፉውን ነገር ለመስማት ንጉሡ ጌታዬ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነውና የጌታዬ የንጉሡ ቃል ያጽናናኛል፤ አምላክህም እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን አልሁ።
18 ፤ ንጉሡም ለሴቲቱ መልሶ። የምጠይቅሽን ነገር አትሰውሪኝ አላት። ሴቲቱም። ጌታዬ ንጉሥ ይናገር አለች።
19 ፤ ንጉሡም። በዚህ ሁሉ የኢዮአብ እጅ ከአንቺ ጋር ነውን? አላት። ሴቲቱም መልሳ። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታዬ ንጉሥ ከተናገረው ነገር ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሊል የሚችል የለም፤ ባሪያህ ኢዮአብ አዝዞኛል፥ ይህንም ቃል ሁሉ በባሪያህ አፍ አደረገው።
20 ፤ ባሪያህ ኢዮአብ የዚህ ነገር መልክ እንዲለወጥ አደረገ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ጠቢብ እንደ ሆነ፥ አንተም ጌታዬ በምድር ላይ ያለውን ነገር ሁሉ ታውቅ ዘንድ ጠቢብ ነህ አለች።
21 ፤ ንጉሡም ኢዮአብን። እነሆ፥ ይህን ነገር አድርጌአለሁ፤ እንግዲህ ሂድና ብላቴናውን አቤሴሎምን መልሰው አለው።
22 ፤ ኢዮአብም በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ እጅ ነሣ፥ ንጉሡንም ባረከ፤ ኢዮአብም። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የባሪያህን ነገር አድርገሃልና በዓይንህ ፊት ሞገስ እንዳገኘ ባሪያህ ዛሬ አወቀ አለ።
23 ፤ ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ ጌሹር ሄደ፥ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም ይዞ መጣ።
24 ፤ ንጉሡም። ወደ ቤቱ ይሂድ እንጂ ፊቴን እንዳያይ አለ፤ አቤሴሎምም ወደ ቤቱ ሄደ፥ የንጉሡንም ፊት አላየም።
25 ፤ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ የተመሰገነ ሰው አልነበረም፤ ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም።
26 ፤ ጠጕሩም ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቈርጠው ነበር፤ ሲቈረጥም የራሱ ጠጕር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዘን ነበር።
27 ፤ ለአቤሴሎምም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት፤ የሴቲቱም ልጅ ስም ትዕማር ነበረ፥ እርስዋም የተዋበች ሴት ነበረች።
28 ፤ አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ የንጉሡን ፊት ሳያይ ተቀመጠ።
29 ፤ አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ይልከው ዘንድ ወደ ኢዮአብ ላከ፥ ወደ እርሱም ሊመጣ አልወደደም፤ ሁለተኛም ላከበት፥ ሊመጣ ግን አልወደደም።
30 ፤ ባሪያዎቹንም። በእርሻዬ አጠገብ ያለውን የኢዮአብን እርሻ እዩ፥ በዚያም ገብስ አለው፤ ሂዳችሁ በእሳት አቃጥሉት አላቸው። የአቤሴሎምም ባሪያዎች እርሻውን አቃጠሉት።
31 ፤ ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ወደ ቤቱ መጣና። ባሪያዎችህ እርሻዬን ስለምን አቃጠሉት? አለው።
32 ፤ አቤሴሎምም ኢዮአብን መልሶ። ከጌሹር ለምን መጣሁ? በዚያም ተቀምጩ ብሆን ይሻለኝ ነበር ብለህ እንድትነግረው ወደ ንጉሡ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ጠራሁህ፤ አሁንም የንጉሡን ፊት ልይ፥ ኃጢአት ቢሆንብኝ ይግደለኝ አለው።
33 ፤ ኢዮአብም ወደ ንጉሥ መጥቶ ነገረው፤ አቤሴሎምንም ጠራው፥ ወደ ንጉሡም ገብቶ በንጉሥ ፊት ወደ ምድር በግምባሩ ተደፋ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።