መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ።. Chapter 23
1 ፤ በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ በረታ፥ የመቶ አለቆቹንም፥ የይሮሐምን ልጅ ዓዛርያስን፥ የይሆሐናንንም ልጅ ይስማኤልን፥ የዖቤድንም ልጅ ዓዛርያስን፥ የዓዳያንም ልጅ መዕሤያን፥ የዝክሪንም ልጅ ኤሊሳፋጥን ወስዶ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ።
2 ፤ ይሁዳንም ዞሩ፥ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሌዋውያንንና የእስራኤልን አባቶች ቤቶች አለቆች ሰብስበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
3 ፤ ጉባኤውም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከንጉሥ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮዳሄም አላቸው። እነሆ፥ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ልጆች እንደተናገረ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል።
4 ፤ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከካህናትና ከሌዋዊውያን ከሦስት አንድ እጅ በመግቢያ በሮች በረኞች ሁኑ፤
5 ፤ ከሦስት አንድ እጅም በንጉሥ ቤት ሁኑ፤ አንድ እጅም በመካከለኛው በር ሁኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ይሁኑ።
6 ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤት ግን ከካህናትና ከአገልጋዮቹ ሌዋውያን በቀር ማንም አይግባ፤ እነርሱ ቅዱሳን ናቸውና ይግቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ የእግዚአብሔርን ሕግ ይጠብቅ።
7 ፤ ሌዋውያንም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን በዙሪያው ይክበቡት፤ ወደ ቤቱም የሚገባ ይገደል ንጉሡም ሲገባና ሲወጣ ከእርሱ ጋር ሁኑ።
8 ፤ ሌዋውያንና ይሁዳም ሁሉ ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ካህኑም ዮዳሄ ሰሞነኞቹን አላሰናበተም ነበርና እያንዳንዱ በሰንበት ቀን ይገቡ የነበሩትን በሰንበትም ቀን ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ወሰደ።
9 ፤ ካህኑም ዮዳሄ በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር አላባሽ አግሬውንም ጋሻ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው።
10 ፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ እየያዘ በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ እንዲቆም አደረገ።
11 ፤ የንጉሡንም ልጅ አውጥተው ዘውዱን ጫኑበት፥ ምስክሩንም ሰጡት፥ አነገሡትም፤ ዮዳሄና ልጆቹም። ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ እያሉ ቀቡት።
12 ፤ ጎቶሊያም የሚሮጡትንና ንጉሡን የሚያመሰግኑትን የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጣች።
13 ፤ እነሆም፥ ንጉሡ በመግቢያው በዓምዱ አጠገብ ሆኖ ከንጉሡ ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ ብሎአቸው መለከቱን ይነፉ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ እያዜሙ የምስጋና መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ጎቶሊያም ልብስዋን ቀድዳ። ዓመፅ ነው፥ ዓመፅ ነው ብላ ጮኸች።
14 ፤ ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች። ወደ ሰልፉ መካከል አውጡአት፤ የሚከተላትም በሰይፍ ይገደል ብሎ አዘዛቸው። ካህኑም። በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ አትግደሉአት አለ።
15 ፤ ገለልም ብለው አሳለፉአት፤ እርስዋም ወደ ፈረሱ በር መግቢያ ወደ ንጉሡ ቤት ሄደች፥ በዚያም ገደሉአት።
16 ፤ ዮዳሄም በእርሱና በሕዝቡ ሁሉ በንጉሡም መካከል የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረገ።
17 ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ በኣል ቤት ሄደው አፈረሱት፥ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም አደቀቁ፥ የበኣልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት።
18 ፤ ዮዳሄም በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው፥ እንደ ዳዊትም ትእዛዝ፥ በደስታና በመዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ዳዊት በእግዚአብሔር ቤት የከፈላቸውን ካህናትና ሌዋውያን በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ላይ ሾመ።
19 ፤ በማናቸውም ነገር ሁሉ ርኩስ የሆነ ሰው እንዳይገባ በእግዚአብሔር ቤት በር በረኞችን አኖረ።
20 ፤ የመቶ አለቆችንም፥ ከበርቴዎቹንም፥ የሕዝቡንም አለቆች፥ የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፥ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወረደ፤ በላይኛውም በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጡ፥ ንጉሡንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አኖሩት።
21 ፤ የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፥ ከተማይቱም ጸጥ አለች፤ ጎቶሊያንም በሰይፍ ገደሉአት። ች