መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ።. Chapter 36

1 ፤ የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወስደው በአባቱ ፋንታ በኢየሩሳሌም አነገሡት።
2 ፤ ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሦስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ።
3 ፤ የግብጽም ንጉሥ በኢየሩሳሌም ከመንግሥቱ አወጣው፥ መቶም መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ዕዳ ጣለበት።
4 ፤ የግብጽም ንጉሥ ወንድሙን ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ፥ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠ፤ ኒካዑም ወንድሙን ኢዮአክስን ይዞ ወደ ግብፅ ወሰደው።
5 ፤ ኢዮአቄምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
6 ፤ የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር በእርሱ ላይ መጥቶ ወደ ባቢሎን ይወስደው ዘንድ በሰንሰለት አሰረው።
7 ፤ ናቡከደነፆርም ከእግዚአብሔር ቤት ዕቃ አያሌውን ወደ ባቢሎን አፈለሰ፥ በባቢሎንም በመቅደሱ ውስጥ አኖረው።
8 ፤ የቀረውም የኢዮአቄም ነገር፥ ያደረገውም ርኵሰት፥ በእርሱም የተገኘው ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፎአል፤ ልጁም ዮአኪን በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
9 ፤ ዮአኪንም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአሥራ ስምንት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወርና አሥር ቀን ነገሠ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ።
10 ፤ ዓመቱ ባለፈ ጊዜ ንጉሡ ናቡከደነፆር ልኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፥ የከበረውንም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃ ከእርሱ ጋር አስወሰደ፤ ወንድሙንም ሴዴቅያስን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠ።
11 ፤ ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ።
12 ፤ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ በእግዚአብሔርም አፍ በተናገረው በነቢዩ በኤርሚያስ ፊት ራሱን አላወረደም።
13 ፤ ደግሞም በእግዚአብሔር አምሎት በነበረው በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤ ወደ እስራኤልም አምላክ ወደ እግዚአብሔር እንዳይመለስ አንገቱን አደነደነ ልቡንም አጠነከረ።
14 ፤ ደግሞም የካህናቱ አለቆች ሁሉ ሕዝቡም እንደ አሕዛብ ያለ ርኵሰት ሁሉ መተላለፍን አበዙ፤ በኢየሩሳሌምም የቀደሰውን የእግዚአብሔርን ቤት አረከሱ።
15 ፤ የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር።
16 ፤ እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፥ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፥ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፥ ቃሉንም ያቃልሉ፥ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።
17 ፤ ስለዚህም የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጕልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ ጕልማሳውንና ቈንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አልማረም፤ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።
18 ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ዕቃ ሁሉ ታላቁንና ታናሹን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት መዝገብ፥ የንጉሡንና የአለቆቹን መዝገብ፥ እነዚህን ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰደ።
19 ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ፥ አዳራሾችዋንም በእሳት አቃጠሉ፥ መልካሙንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፉ።
20 ፤ ከሰይፍም ያመለጡትን ወደ ባቢሎን ማረካቸው፤ የፋርስ ንጉሥም እስኪነግሥ ድረስ ለንጉሡና ለልጆቹ ባሪያዎች ሆኑ፤
21 ፤ በኤርምያስም አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል እንዲፈጸም፥ ምድሪቱ ሰንበትን በማድረግዋ እስክታርፍ ድረስ፤ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ፥ ሰባ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ፥ ሰንበትን አገኘች።
22 ፤ በኤርምያስም አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እርሱም። የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል።
23 ፤ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል፤ ከሕዝቡ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ማንም ቢሆን አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሁን፥ እርሱም ይውጣ ብሎ በመንግሥቱ ሁሉ አዋጅ አስነገረ፥ ደግሞም በጽሕፈት አደረገው።