መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ።. Chapter 14
1 ፤ አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በእርሱም ዘመን ምድሪቱ አሥር ዓመት ያህል ዐረፈች።
2 ፤ አሳም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን ነገር አደረገ፤
3 ፤ የእንግዶቹንም አማልክት መሠዊያ የኮረብታውንም መስገጃዎች አፈረሰ፥ ሐውልቶቹንም ሰበረ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤
4 ፤ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ፥ ሕጉንና ትእዛዙንም ያደርጉ ዘንድ ይሁዳን አዘዘ።
5 ፤ ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችና የፀሐይ ምስሎችን አስወገደ፤ መንግሥቱም በእርሱ ሥር በሰላም ተቀመጠች።
6 ፤ በይሁዳም ምሽጎች ከተሞችን ሠራ፤ እግዚአብሔርም ዕረፍት ስለ ሰጠው ምድሪቱ ጸጥ ብላ ነበር፥ በዚያም ዘመን ሰልፍ አልነበረም።
7 ፤ ይሁዳንም። እነዚህን ከተሞች እንሥራ፥ ቅጥርም ግንብም መዝጊያም መወርወሪያም እናድርግባቸው፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ ገና በፊታችን ናት፤ እኛ ፈልገነዋል፥ እርሱም በዙሪያችን ዕረፍት ሰጥቶናል አለ። እነርሱም ሠሩ አከናወኑም።
8 ፤ ለአሳም አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት፥ ጋሻም የሚሸከሙ ቀስትም የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ።
9 ፤ ኢትዮጵያዊውም ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው፤ ወደ መሪሳም መጣ።
10 ፤ አሳም ሊጋጠመው ወጣ፥ በመሪሳም አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆ ውስጥ ተሰለፉ።
11 ፤ አሳም። አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህም፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ፥ በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና እርዳን፤ አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህ ብሎ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
12 ፤ እግዚአብሔርም በአሳና በይሁዳ ፊት ኢትዮጵያውያንን መታ፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ።
13 ፤ አሳም ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌራራ ድረስ አሳደዱአቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ፥ በእግዚአብሔርና በሠራዊቱ ፊት ተሰባብረዋልና፤ እጅግም ብዙ ምርኮ ወሰዱ።
14 ፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ስለ ወደቀባቸው በጌራራ ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ መቱ፤ በከተሞቹም ውስጥ እጅግ ብዝበዛ ነበረና ከተሞቹን ሁሉ በዘበዙ።
15 ፤ የከብቶቹንም በረት አፈረሱ፤ እጅግም ብዙ በጎችንና ግመሎችንም ማረኩ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ።