መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን. Chapter 4
1 ፤ ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ዓይኖችሽ እንደ ርግቦች ናቸው፤ ጠጕርሽ በገለዓድ ተራራ እንደሚወርድ እንደ ፍየል መንጋ ነው።
2 ፤ ጥርሶችሽ ታጥበው እንደ ተሸለቱ ሁሉም መንታ እንደ ወለዱ ከእነርሱም መካን እንደሌለባቸው መንጎች ናቸው።
3 ፤ ከንፈሮችሽ እንደ ቀይ ሐር ፈትል ናቸው፥ አፍሽም ያማረ ነው፤ በዓይነ ርግብ መሸፈኛሽ ውስጥ ጕንጭና ጕንጭሽ እንደ ተከፈለ ሮማን ናቸው።
4 ፤ አንገትሽ ለሰልፍ ዕቃ መስቀያ እንደ ተሠራው እንደ ዳዊት ግንብ ነው፤ ሺህ ጋሻ የኃያላንም መሣሪያ ሁሉ ተንጠልጥሎበታል።
5 ፤ ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ እንደ ተወለዱ፥ በሱፍ አበባ መካከል እንደሚሰማሩ እንደ ሚዳቋ ግልገሎች ናቸው።
6 ፤ ቀኑ እስኪነፍስ ጥላውም እስኪያልፍ ድረስ፥ ወደ ከርቤው ተራራ ወደ ዕጣኑም ኮረብታ እሄዳለሁ።
7 ፤ ወዳጄ ሆይ፥ ሁለንተናሽ ውብ ነው፥ ነውርም የለብሽም።
8 ፤ ሙሽራዬ ሆይ፥ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤ ከአማና ራስ ከሳኔርና ከኤርሞን ራስ፥ ከአንበሶች መኖሪያ ከነብሮችም ተራራ ተመልከች።
9 ፤ እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ልቤን በደስታ አሳበድሽው፤ አንድ ጊዜ በዓይኖችሽ፥ ከአንገትሽ ድሪ በአንዱ ልቤን በደስታ አሳበድሽው።
10 ፤ እኅቴ ሙሽራ ሆይ፥ ፍቅርሽ እንዴት መልካም ነው! ፍቅርሽ ከወይን ጠጅ ይልቅ እንዴት ይሻላል! የዘይትሽም መዓዛ ከሽቱ ሁሉ!
11 ፤ ሙሽራዬ ሆይ፥ ከከንፈሮችሽ ማር ይንጠበጠባል፤ ከምላስሽ በታች ማርና ወተት አለ፥ የልብስሽም መዓዛ እንደ ሊባኖስ ሽታ ነው።
12 ፤ እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈ ገነት፥ የተዘጋ ምንጭ የታተመም ፈሳሽ ናት።
13 ፤ ቡቃያሽ ሮማንና የተመረጠ ፍሬ፥ ቆዕ ከናርዶስ ጋር ያለበት ገነት ነው፥
14 ፤ ናርዶስ ከቀጋ ጋር፥ የሽቱ ሣርና ቀረፋ፥ ከልዩ ልዩ ዕጣን ጋር፥ ከርቤና እሬት ከክቡር ሽቱ ሁሉ ጋር።
15 ፤ አንቺ የገነት ምንጭ፥ የሕይወት ውኃ ጕድጓድ፥ ከሊባኖስም የሚፈስስ ወንዝ ነሽ።
16 ፤ የሰሜን ነፋስ ሆይ፥ ተነሥ፥ የደቡብም ነፋስ ና፤ በገነቴ ላይ ንፈስ፥ ሽቱውም ይፍሰስ፤ ውዴ ወደ ገነቱ ይግባ፥ መልካሙንም ፍሬ ይብላ።