መዝሙረ ዳዊት. Chapter 69
1 ለመዘምራን አለቃ፤ በመለከቶች፤ የዳዊት መዝሙር።1 አቤቱ፥ ውኃ እስከ ነፍሴ ደርሶብኛልና አድነኝ።
2 በጥልቅ ረግረግ ጠለቅሁ መቋሚያም የለኝም። ወደ ጥልቅ ባሕር ገባሁ ማዕበልም አሰጠመኝ።
3 በጩኸት ደከምሁ ጕሮሮዬም ሰለለ፤ አምላኬን ስጠብቅ ዓይኖቼ ፈዘዙ።
4 በከንቱ የሚጠሉኝ ከራሴ ጠጕር በዙ፤ በዓመፅ ያሚያሳድዱኝ ጠላቶቼ በረቱ፤ በዚያን ጊዜ ያልቀማሁትን መለስሁ።
5 አቤቱ፥ አንተ ስንፍናዬን ታውቃለህ፥ ኃጢአቴም ከአንተ አልተሰወረም።
6 አቤቱ የሠራዊት አምላክ፥ ተስፋ የሚያደርጉህ በእኔ አይፈሩ፤ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ የሚሹህ በእኔ አይነወሩ።
7 ስለ አንተ ስድብን ታግሻለሁና፥ እፍረትም ፊቴን ሸፍናለችና።
8 ለወንድሞቼ እንደ ሌላ፥ ለእናቴ ልጆችም እንደ እንግዳ ሆንሁባቸው፥
9 የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፥ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቆአልና።
10 ነፍሴን በጾም አስመረርሁአት፥ ለስድብም ሆነብኝ።
11 ማቅ ለበስሁ ምሳሌም ሆንሁላቸው።
12 በደጅ የሚቀመጡ በእኔ ይጫወታሉ፤ ወይን የሚጠጡ እኔን ይዘፍናሉ።
13 አቤቱ፥ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፤ አቤቱ፥ በምሕረትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ።
14 እንዳይውጠኝ ከረግረግ አውጣኝ፤ ከሚጠሉኝና ከጥልቅ ውኃ አስጥለኝ።
15 የውኃው ማዕበል አያስጥመኝ፥ ጥልቁም አይዋጠኝ፥ ጕድጓድም አፉን በእኔ ላይ አይዝጋ።
16 አቤቱ፥ ምሕረትህ መልካም ናትና ስማኝ። እንደ ርኅራኄህም ብዛት ወደ እኔ ተመልከት፤
17 ከባሪያህም ፊትህን አትሰውር፤ ተጨንቄአለሁና ፈጥነህ አድምጠኝ።
18 ነፍሴን ተመልክተህ ተቤዣት፤ ስለ ጠላቶቼም አድነኝ።
19 አንተ ስድቤን እፍረቴንም ነውሬንም ታውቃለህ፤ የሚያስጨንቁኝ ሁሉ በፊትህ ናቸው።
20 ነፍሴ ስድብንና ኃሣርን ታገሠች፤ አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም። የሚያጽናናኝም አጣሁ።
21 ለመብሌ ሐሞት ሰጡኝ፥ ለጥማቴም ሆምጣጤ አጠጡኝ።
22 ማዕዳቸው በፊታቸው ለወጥመድ ለፍዳ ለዕንቅፋት ትሁንባቸው፤
23 ዓይኖቻቸው እንዳያዩ ይጨልሙ፥ ጀርባቸውም ዘወትር ይጕበጥ።
24 መዓትህን በላያቸው አፍስስ፥ የቍጣህ መቅሠፍትም ያግኛቸው።
25 ማደሪያቸው በረሃ ትሁን፥ በድንኳኖቻቸውም የሚቀመጥ አይገኝ፤
26 አንተ የቀሠፍኸውን እነርሱ አሳድደዋልና፥ በቍስሌም ላይ ጥዝጣዜ ጨመሩብኝ።
27 በኃጢአታቸው ላይ ኃጢአትን ጨምርባቸው፥ በጽድቅህም አይግቡ።
28 ከሕያዋን መጽሐፍ ይደምሰሱ፥ ከጻድቃንም ጋር አይጻፉ።
29 እኔ ችግረኛና ቍስለኛ ነኝ፤ አቤቱ፥ የፊትህ መድኃኒት ይቀበለኝ።
30 የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አመሰግናለሁ፥ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።
31 ቀንድና ጥፍር ካበቀለ ከእምቦሳ ይልቅ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋል።
32 ችግረኞች ያያሉ ደስ ይላቸዋል፤ እግዚአብሔርን ፈልጉ ሕያዋንም ሁኑ።
33 እግዚአብሔር ችግረኞችን ሰምቶአልና፥ እስረኞቹንም አልናቀምና።
34 ሰማይና ምድር ባሕርም በእርስዋም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመሰግኑታል።
35 እግዚአብሔር ጽዮንን ያድናታልና፥ የይሁዳንም ከተሞች ይሠራልና፤ በዚያም ይቀመጣሉ ይወርሱአትማል።
36 የባሪያዎቹ ዘር ይኖሩባታል። ስሙንም የሚወድዱ በዚያ ይቀመጣሉ።