መዝሙረ ዳዊት. Chapter 76
1 ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ስለ አሦራውያን፤ የአሳፍ የምስጋና መዝሙር።1 እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ፥ ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው።
2 ስፍራው በሳሌም፥ ማደሪያውም በጽዮን ነው።
3 በዚያም የቀስትን ኃይል፥ ጋሻን ሰይፍን ሰልፍንም ሰበረ፤ በዚያም ቀንዶችን ሰበረ።
4 አንተ በዘላለም ተራሮች ሆነህ በድንቅ ታበራለህ።
5 ልበ ሰነፎች ሁሉ ደነገጡ፥ እንቅልፋቸውንም አንቀላፉ፤ ባለጠጎች ሁሉ በእነርሱ እጅ ምንም አላገኙም።
6 የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ ከተግሣጽህ የተነሣ ፈረሰኞች ሁሉ አንቀላፉ።
7 አንተ ግን፥ አንተ ግሩም ነህ፤ ቍጣህን ማን ይቃወማል?
8 ፍርድን ከሰማይ አሰማህ፤ ምድር ፈራች ዝምም አለች፥
9 ልበ የዋሃን ያድን ዘንድ እግዚአብሔር ለፍርድ በተነሣ ጊዜ።
10 ሰው በፈቃዱ ያመሰግንሃልና፥ ከሕሊናቸው ትርፍም በዓልህን ያደርጋሉ።
11 ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ስእለትን ክፈሉ፤ በዙሪያው ያሉ ሁሉ እጅ መንሻን ለሚያስፈራው ያገባሉ።
12 የመኳንንትን ነፍስ ያወጣል፤ በምድርም ነገሥታት ዘንድ ያስፈራል።