መዝሙረ ዳዊት. Chapter 99
1 የዳዊት መዝሙር።1 እግዚአብሔር ነገሠ፥ አሕዛብ ይደንግጡ፤ በኪሩቤል ላይ ተቀመጠ፥ ምድር ትናወጥ።
2 እግዚአብሔር በጽዮን ታላቅ ነው፤ እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ አለ።
3 ግሩምና ቅዱስ ነውና ሁሉ ታላቅ ስምህን ያመስግኑ።
4 የንጉሥ ክብር ፍርድን ይወድዳል፤ አንተ ቅንነትን አጸናህ፥ ለያዕቆብ ፍርድንና ጽድቅን አንተ አደረግህ።
5 አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ ቅዱስ ነውና ወደ እግሩ መረገጫ ስገዱ።
6 ሙሴና አሮን በካህናቱ ዘንድ፥ ሳሙኤልም ስሙን በሚጠሩት ዘንድ ናቸው። እግዚአብሔርን ጠሩት፥ እርሱም መለሰላቸው።
7 በደመና ዓምድም ተናገራቸው፤ ምስክሩንና የሰጣቸውን ትእዛዝ ጠበቁ።
8 አቤቱ አምላክችን ሆይ፥ አንተ ሰማሃቸው፤ አቤቱ፥ አንተ ማርሃቸው፥ ሥራቸውን ሁሉ ግን ተበቀልሃቸው።
9 አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፥ በቅዱስ ተራራውም ስገዱ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና።