መዝሙረ ዳዊት. Chapter 19
1 ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።1 ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።
2 ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች።
3 ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም።
4 ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።
5 በእነርሱም ውስጥ የፀሐይን ድንኳን አደረገ፥ እርሱም እንደ ሙሽራ ከእልፍኙ ይወጣል፤ እንደ አርበኛ በመንገዱ ለመሮጥ ደስ ይለዋል።
6 አወጣጡ ከሰማያት ዳርቻ ነው፥ ዙረቱም እስከ ዳርቻቸው ነው፤ ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም።
7 የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል።
8 የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፥ ዓይንንም ያበራል።
9 የእግዚአብሔር ፍርሃት ንጹሕ ነው፤ ለዘላለም ይኖራል፤ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ነው።
10 ከወርቅና ከክቡር ዕንቍ ይልቅ ይወደዳል፤ ከማርና ከማር ወለላም ይጣፍጣል።
11 ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል፤ በመጠበቁም እጅግ ይጠቀማል።
12 ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ።
13 የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ።
14 አቤቱ፥ ረድኤቴ መድኃኒቴም፥ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን።