መዝሙረ ዳዊት. Chapter 141
1 የዳዊት መዝሙር።1 አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ ስማኝ፤ ወደ አንተ ስጮኽም የልመናዬን ቃል አድምጥ።
2 ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።
3 አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ።
4 ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው፥ ዓመፃን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሰጥ፤ ከምርጦቻቸውም ጋር አልተባበር።
5 ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፥ ይዝለፈኝም፥ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ፤ ጸሎቴ ገና በክፋታቸው ላይ ነውና።
6 ኃያላኖቻቸው በዓለት አጠገብ ተጣሉ፤ ጣፋጭ ናትና ቃሌን ይሰማሉ።
7 በምድር ላይ እንደ ተሰነጠቀ እንደ መሬት ጓል፥ እንዲሁ አጥንቶቻችን በሲኦል ተበተኑ።
8 አቤቱ ጌታ፥ ዓይኖቼ ወደ አንተ ናቸውና፤ በአንተ ታመንሁ፥ ነፍሴን አታውጣት።
9 ከሰወሩብኝ ወጥመድ፥ ዓመፅንም ከሚያደርጉ ሰዎች ዕንቅፋት ጠብቀኝ።
10 እኔ ብቻዬን እስካልፍ ድረስ ኃጢአተኞች በወጥመዳቸው ይውደቁ።