መዝሙረ ዳዊት. Chapter 140
1 ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።1-2 አቤቱ፥ ከክፉ ሰው አድነኝ፥ በልባቸውም ክፉ ካሰቡ ከዓመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ፤ ቀኑን ሁሉ ለሰልፍ ይከማቻሉ።
3 ምላሳቸውን እንደ እባብ ሳሉ፤ ከከንፈራቸው በታች የእፉኝት መርዝ ነው።
4 አቤቱ፥ ከኃጢአተኞች እጅ ጠብቀኝ፥ እርምጃዬንም ሊያሰናክሉ ከመከሩ ከዓመፀኞች አድነኝ።
5 ትዕቢተኞች ወጥመድን ሰወሩብኝ፥ ለእግሮቼም የወጥመድ ገመድን ዘረጉ፤ በመንገድ ዕንቅፋትን አኖሩ።
6 እግዚአብሔርንም። አንተ አምላኬ ነህ፤ የልመናዬን ቃል፥ አቤቱ፥ አድምጥ አልሁት።
7 አቤቱ፥ ጌታዬ፥ የመድኃኒቴ ጕልበት፥ በሰልፍ ቀን ራሴን ሸፈንህ።
8 አቤቱ፥ ከምኞቴ የተነሣ ለኃጢአተኞች አትስጠኝ፤ በላዬ ተማከሩ፤ እንዳይጓደዱ አትተወኝ።
9 የሚከብቡኝን ራስ የከንፈራቸው ክፋት ይክደናቸው።
10 የእሳት ፍም በላያቸው ይውደቅ፤ እንዳይነሡም ወደ እሳትና ወደ ማዕበል ይጣሉ።
11 ተናጋሪ ሰው በምድር ውስጥ አይጸናም፤ ዓመፀኛን ሰው ክፋት ለጥፋት ይፈልገዋል።
12 እግዚአብሔር ለድሀ ዳኝነትን ለችግረኛም ፍርድን እንዲያደርግ አወቅሁ።
13 ጻድቃንም በእውነት ስምህን ያመሰግናሉ፤ ቀኖችም በፊትህ ይኖራሉ።