መዝሙረ ዳዊት. Chapter 14
1 ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። ሰነፍ በልቡ። አምላክ የለም ይላል። በሥራቸው ረከሱ፥ ጐስቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም።
2 የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ።
3 ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም።
4 ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፥ በምላሳቸው ሸነገሉ፤
5 ከከንፈራቸው በታች የእባብ መርዝ አለ፤ አፋቸው መርገምንና መራራን ተሞልቶአል፤
6 ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ ጥፋትና ጕስቍልና በመንገዳቸው አለ፥ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና፤ እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም።
7 ሕዝቤን እንደ እንጀራ የሚበሉ ኃጢአት የሚሠሩ ሁሉ በውኑ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም።[8] በዚያ በታላቅ ፍርሃት እጅግ ፈሩ፥ እግዚአብሔር በጻድቃን ትውልድ ዘንድ ነውና።[9] የድሆችን ምክር አሳፈራችሁ፥ እግዚአብሔር ግን ተስፋቸው ነው።[10] ከጽዮን መድኃኒትን ለእስራኤል ማን ይሰጣል? እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ያዕቆብ ደስ ይለዋል፥ እስራኤልም ሐሤት ያደርጋል።