መዝሙረ ዳዊት. Chapter 59

1 ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። ሳኦል ይገድሉት ዘንድ ቤቱን እንዲጠብቁ በላከ ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ።1 አምላኬ ሆይ፥ ከጠላቶቼ አድነኝ፤ በላዬም ከቆሙት አስጥለኝ።
2 ከግፍ አድራጊዎች ታደገኝ፥ ከደም ሰዎችም አድነኝ።
3 እነሆ፥ ነፍሴን ሸምቀውባታልና፥ ብርቱዎችም በላዬ ተሰበሰቡ። አቤቱ፥ በበደሌም አይደለም፥ በኃጢአቴም አይደለም።
4 ያለ በደል ሮጥሁ ተዘጋጀሁም፤ ተነሥ፥ ተቀበለኝ፥ እይም።
5 አንተም አቤቱ፥ የኃያላን አምላክ፥ የእስራኤል አምላክ፥ አሕዛብን ሁሉ ትጐበኛቸው ዘንድ ተነሥ፤ ዓመፅ የሚያደርጉትን ሁሉ አትማራቸው።
6 ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ።
7 እነሆ፥ በአፋቸው አሰምተው ይናገራሉ፤ ሰይፍም በከንፈሮቻቸው አለ፤ ማን ይሰማል? ይላሉ።
8 አንተ ግን አቤቱ፥ ትሥቅባቸዋለህ፥ አሕዛብንም ሁሉ ትንቃቸዋለህ።
9 እግዚአብሔር መጠጊያዬ ነውና ኃይሌን ወደ አንተ አስጠጋለሁ።
10 የአምላኬ ቸርነቱ ይገናኘኛል አምላኬ በጠላቶቼ ላይ ያሳየኛል።
11 ሕግህን እንዳይረሱ አትግደላቸው፤ አቤቱ ጋሻዬ፥ በኃይልህ በትናቸው አውርዳቸውም።
12 ስለ አፋቸው ኃጢአት ስለ ከንፈራቸውም ቃል፥ መርገምንና ሐሰትን ስለሚናገሩ፥ በትዕቢታቸው ይጠመዱ።
13 በቍጣ አጥፋቸው፥ እንዳይኖሩም አጥፋቸው፤ የያዕቆብም አምላክ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንዲገዛ ይወቁ።
14 ማታ ይመለሱ እንደ ውሾችም ይራቡ፥ በከተማም ይዙሩ።
15 እነርሱም መብል ለመፈለግ ይበተኑ፤ ያልጠገቡ እንደ ሆነም ያንጐረጕራሉ።
16 እኔ ግን ለኃይልህ እቀኛለሁ፤ በምሕረትህም ማልዶ ደስ ይለኛል፤ በመከራዬ ቀን መጠጊያዬና አምባዬ ሆነኸኛልና።
17 ረዳቴ ሆይ፥ ለአንተ ለአምላኬ እዘምራለሁ፤ አንተ፥ አምላኬ፥ መጠጊያዬ ምሕረቴም ነህና።