መዝሙረ ዳዊት. Chapter 55
1 ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የዳዊት ትምህርት።1 አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ ልመናዬንም ቸል አትበል።
2 ተመልከተኝ ስማኝም። በኀዘኔ ተቅበዘበዝሁ ተናወጥሁም፤
3 ከጠላት ድምፅ ከዓመፀኛም ግፍ የተነሣ፤ ዓመፃን በላዬ ጥለውብኛልና፥ በቁጣም ጠልተውኛልና።
4 ልቤ በላዬ ተናወጠብኝ፥ የሞት ድንጋጤም ወደቀብኝ።
5 ፍርሃትና እንቅጥቅጥ መጡብኝ፥ ጨለማም ሸፈነኝ።
6 በርሬ ዐርፍ ዘንድ እንደ ርግብ ክንፍን ማን በሰጠኝ!
7 እነሆ፥ ኰብልዬ በራቅሁ በምድረ በዳም በተቀመጥሁ፤
8 ከዐውሎና ከብርቱ ንፋስ ሸሽቼ በፈጠንሁ አልሁ።
9 አቤቱ፥ ግፍንና ጠብን በከተማ ውስጥ አይቼአለሁና አስጥማቸው እንደበታቸውንም ቍረጥ።
10 በቀንና በሌሊት በቅጥርዋ ይከብቡአታል፤ ዓመፃና ድካም ኃጢአትም በመካከልዋ ነው፤
11 ተንኰልና ሽንገላ ከአደባባይዋ አይርቁም።
12 ጠላትስ ቢሰድበኝ፥ በታገሥሁ ነበር፤ የሚጠላኝም ራሱን በላዬ ከፍ ከፍ ቢያደርግ፥ ከእርሱ በተሸሸግሁ ነበር።
13 አንተ ግን፥ እኩያዬ ሰው፥ ባልንጀራዬና የልቤ ወዳጅ፤
14 መብልን ከእኔ ጋር በአንድነት ያጣፈጥህ፤ በአንድ ልብ በእግዚአብሔር ቤት ተራመድን።
15 ሞት ይምጣባቸው፤ በሕይወት ሳሉ ወደ ሲኦል ይውረዱ፤ ክፋት በማደሪያቸውና በመካከላቸው ነውና።
16 እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ እግዚአብሔርም ሰማኝ።
17 በማታና በጥዋት በቀትርም እናገራለሁ እጮኽማለሁ፥ ቃሌንም ይሰማኛል።
18 በእኔ ላይ ብዙ ነበሩና ከሚቃረቡኝ ነፍሴን በሰላም አድናት።
19 ቤዛ የላቸውምና፥ እግዚአብሔርንም አልፈሩትምና ከጥንት ጀምሮ የነበረ እግዚአብሔር ሰምቶ ያጐሰቍላቸዋል።
20 ከእርሱ ጋር ሰላም በነበሩት ላይ እጁን ዘረጋ፤ ኪዳኑንም አረከሱ።
21 አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ፥ በልቡ ግን ሰልፍ ነበረ፤ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ፥ እነርሱ ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው።
22 ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፥ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።
23 አንተ ግን፥ አቤቱ፥ ወደ ሞት ጕድጓድ ታወርዳቸዋለህ፤ የደም ሰዎችና ሸንጋዮች ዘመናቸው ግማሽ አይሞላም፤ እኔ ግን፥ አቤቱ፥ እታመንሃለሁ።