መጽሐፈ ምሳሌ. Chapter 30
1 የማሣ አገር ሰው የያቄ ልጅ የአጉር ቃል ሰውየው ለኢቲኤልና ለኡካል እንደዚህ ይናገራል።
2 እኔ በእውነት ከሰው ሁሉ ይልቅ ደንቆሮ ነኝ፥ የሰውም ማስተዋል የለብኛም።
3 ጥበብንም አልተማርሁም፥ ቅዱሱንም አላወቅሁትም።
4 ወደ ሰማይ የወጣ የወረደስ ማን ነው? ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደ ሆንህ፥ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው?
5 የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ ተፈትናለች፤ እርሱ ለሚታመኑት ጋሻ ነው።
6 እንዳይዘልፍህ፥ ሐሰተኛም እንዳትሆን በቃሉ አንዳች አትጨምር።
7 ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ፤
8 ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፤ ድኅነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥
9 እንዳልጠግብ እንዳልክድህም። እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።
10 እንዳይሰድብህ በደለኛም እንዳትሆን ባሪያን በጌታው ፊት አትማ።
11 አባቱን የሚረግም፥ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ አለ።
12 ለራሱ ንጹሕ የሆነ የሚመስለው ከርኵሰቱ ያልጠራ ትውልድ አለ።
13 ከፍ ከፍ ያሉ ዓይኖች ያሉት፥ ሽፋሽፍቶቹም ወደ ላይ የሚያዩ ትውልድ አለ።
14 ድሆችን ከምድር ላይ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ያጠፋና ይጨርስ ዘንድ ጥርሶቹ ሰይፍ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ አለ።
15 አልቅት። ስጠን ስጠን የሚሉ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉት። ሦስቱ የማይጠግቡ አራቱም። በቃን የማይሉ ናቸው፤
16 እነርሱም ሲኦልና የማትወልድ ማኅፀን ውኃ የማትጠግብ ምድርና። በቃኝ የማትል እሳት ናቸው።
17 በአባትዋ የምታላግጥን የእናትዋንም ትእዛዝ የምትንቅን ዓይን የሸለቆ ቍራዎች ይጐጠጕጡአታል፥ አሞራዎችም ይበሉአታል።
18 ሦስት ነገር ይገርመኛል፥ አራተኛውንም ከቶ አላስተውለውም።
19 እነርሱም የንስር መንገድ በሰማይ፥ የእባብ መንገድ በድንጋይ ላይ፥ የመርከብ መንገድ በባሕር ላይ፥ የሰውም መንገድ ከቈንጆ ጋር ናቸው።
20 እንዲሁ በልታ አፍዋን የምታብስ። አንዳች ክፉ ነገር አላደረግሁም የምትልም የአመንዝራ ሴት መንገድ ናት።
21 በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፥ አራተኛውንም ትሸከም ዘንድ አይቻላትም።
22 ባሪያ በነገሠ ጊዜ ሰነፍም እንጀራ በጠገበ ጊዜ፥
23 የተጠላች ሴት ባል ባገኘች ጊዜ፥ ሴት ባሪያም እመቤቷን በወረሰች ጊዜ።
24 በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፤ እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው፤
25 ገብረ ጕንዳን ኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው፥ ነገር ግን በበጋ መኖዋቸዋን ይሰበስባሉ።
26 ሽኮኮዎች ያልበረቱ ሕዝቦች ናቸው፥ ቤታቸውን ግን በቋጥኝ ድንጋይ ውስጥ ያደርጋሉ።
27 አንበጣዎች ንጉሥ የላቸውም፥ ሁላቸው ግን በመልካም ሥርዓት ይሄዳሉ።
28 እንሽላሊት በእጅ ይያዛል፥ በነገሥታት ግቢ ግን ይኖራል።
29 መልካም አረማመድን የሚራመዱ ሦስት ፍጥረቶች አሉ፥ አራተኛውም መልካም አካሄድን ይሄዳል፤
30 የአንበሳ ደቦል ከእንስሳ ሁሉ የሚበረታ፥ የማይመለስ፥ እንስሳንም የማይፈራ፤
31 በእንስቶች መካከል በድፍረት የሚራመድ አውራ ዶሮ፤ መንጋን የምመራ አውራ ፍየል፤ በሕዝብ ፊት በግልጥ የሚናገር ንጉሥ።
32 ከፍ ከፍ ስትል ስንፍናን ያደረግህ እንደሆነ፥ ክፉም ያሰብህ እንደ ሆነ፥ እጅህን በአፍህ ላይ ጫን።
33 ወተት መግፋት ቅቤን ያወጣል፥ አፍንጫንም መጭመቅ ደምን ያወጣ፤ እንዲሁም ቍጣን መጐተት ጠብን ያወጣል።