መጽሐፈ ምሳሌ. Chapter 13
1 ባለ አእምሮ ልጅ የአባቱን ተግሣጽ ይሰማል። ፌዘኛ ግን ተግሣጽን አይሰማም።
2 ሰው ከአፉ ፍሬ መልካምን ይበላል፤ የዓመፀኞች ነፍስ ግን ግፍን ትሻለች።
3 አፉን የሚጠብቅ ነፍሱን ይጠብቃል፤ ከንፈሩን የሚያሞጠሙጥ ግን ጥፋትን ያገኘዋል።
4 የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም፤ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች።
5 ጻድቅ ሐሰትን ይጠላል፤ ኀጥእ ግን ያሳፍራል ያስነውራልም።
6 በመንገዱ ያለ ነውር የሚሄደውን ጽድቅ ይጠብቀዋል፤ ኃጢአት ግን ኃጢአተኛውን ይጥለዋል።
7 ራሱን ባለጠጋ የሚያስመስል ሰው አለ፥ ነገር ግን አንዳች የለውም፤ ራሱን ድሀ የሚያስመስል አለ፥ ነገር ግን እጅግ ባለጠግነት አለው።
8 ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው፤ ድሀ ግን ተግሣጽን አይሰማም።
9 ሁልጊዜ ለጻድቃን ብርሃን ነው፤ የኀጥኣን መብራት ግን ይጠፋል።
10 በትዕቢት ጠብ ብቻ ይሆናል፤ ጥበብ ግን ምክርን በሚቀበሉ ዘንድ ናት።
11 በችኰላ የምትከማች ሀብት ትጐድላለች፤ ጥቂት በጥቂት የተከማቸች ግን ትበዛለች።
12 የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት።
13 ትእዛዝን የሚያቃልል በትእዛዝ ተይዞ ይጠፋል፤ ትእዛዝን የሚፈራ ግን በደኅንነት ይኖራል።
14 ሰው ከሞት ወጥመድ ያመልጥ ዘንድ የጠቢብ ሰው ትምህርት የሕይወት ምንጭ ነው።
15 መልካም እውቀት ሞገስን ይሰጣል፤ የወስላቶች መንገድ ግን ሸካራ ናት።
16 ብልህ ሁሉ በእውቀት ይሠራል፤ ሰነፍ ግን ስንፍናውን ይገልጣል።
17 መጥፎ መልእክተኛ በክፉ ላይ ይወድቃል፤ የታመነ መልእክተኛ ግን ፈውስ ነው።
18 ድህነትና ነውር ተግሣጽን ቸል ለሚሉ ነው፤ ዘለፋን የሚሰማ ግን ይከብራል።
19 የተፈጸመች ፈቃድ ሰውነትን ደስ ታሰኛለች፤ ሰነፎች ግን ከክፉ መራቅን ይጸየፋሉ።
20 ከጠቢባን ጋር የሚሄዱ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።
21 ክፉ ነገር ኃጢአተኞችን ያሳድዳቸዋል፤ ጻድቃን ግን መልካሙን ዋጋ ይቀበላሉ።
22 ጻድቅ ሰው ለልጅ ልጆቹ ያወርሳል፤ የኃጢአተኛ ብልጥግና ግን ለጻድቅ ትጠበቃለች።
23 በድሆች እርሻ ላይ ብዙ ሲሳይ አለ፤ ከፍርድ መጕደል የተነሣ ግን ይጠፋል።
24 በበትር ከመምታት የሚራራ ሰው ልጁን ይጠላል፤ ልጁን የሚወድድ ግን ተግቶ ይገሥጻዋል።
25 ጻድቅ ሰውነቱ እስክትጠግብ ድረስ ይበላል፤ የኀጥኣን ሆድ ግን ይራባል።