መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ።. Chapter 15
1 ፤ ዳዊትም በከተማው ላይ ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔርም ታቦት ስፍራ አዘጋጀ፥ ድንኳንም ተከለለት።
2 ፤ በዚያን ጊዜም ዳዊት። የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከሙ ዘንድ፥ ለዘላለሙም ያገለግሉት ዘንድ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከም ዘንድ አይገባውም አለ።
3 ፤ ዳዊትም ወዳዘጋጀለት ስፍራ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ እስራኤልን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ።
4 ፤ ዳዊትም የአሮንን ልጆችና ሌዋውያንን ሰበሰበ።
5 ፤ ከቀዓት ልጆች፤ አለቃው ኡርኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሀያ፤
6 ፤ ከሜራሪ ልጆች፤ አለቃው ዓሣያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ ሀያ፤
7 ፤ ከጌድሶን ልጆች፤ አለቃው ኢዮኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሠላሳ፤
8 ፤ ከኤሊጻፋን ልጆች፤ አለቃው ሸማያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ፤
9 ፤ ከኬብሮን ልጆች፤ አለቃው ኤሊኤል፥ ወንድሞቹም ሰማንያ፤
10 ፤ ከዑዝኤል ልጆች፤ አለቃው አሚናዳብ፥ ወንድሞቹም መቶ አሥራ ሁለት።
11 ፤ ዳዊትም ካህናቱን ሳዶቅንና አቢያታርን፥ ሌዋውያንንም ኡርኤልን፥ ዓሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሸማያን፥ ኤሊኤልን፥ አሚናዳብንም ጠርቶ።
12 ፤ እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤቶች አለቆች ናችሁ፤ ወዳዘጋጀሁለት ስፍራ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ታመጡ ዘንድ እናንተና ወንድሞቻችሁ ተቀደሱ።
13 ፤ ቀድሞም አልተሸከማችሁምና፥ እንደ ሥርዓቱም አልፈለግነውምና አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን ስብራት አደረገ አላቸው።
14 ፤ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጡ ዘንድ ካህናቱና ሌዋውያኑ ተቀደሱ።
15 ፤ ሙሴም እንዳዘዘው እንደ እግዚአብሔር ቃል የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ።
16 ፤ ዳዊትም በዜማ ዕቃ በመሰንቆና በበገና በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን ወንድሞቻቸውን ይሾሙ ዘንድ ለሌዋውያን ኣለቆች ተናገረ።
17 ፤ ሌዋውያኑም የኢዮኤልን ልጅ ኤማንን፥ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፥ ከወንድሞቻቸውም ከሜራሪ ልጆች የቂሳን ልጅ ኤታንን፥
18 ፤ ከእነርሱም ጋር በሁለተኛው ተራ የሆኑትን ወንድሞቻቸውን ዘካርያስን፥ ቤንን፥ ያዝኤልን፥ ሰሚራሞትን፥ ይሒኤልን፥ ዑኒን፥ ኤልያብን፥ በናያስን፥ መዕሤያን፥ መቲትያን፥ ኤሊፍሌሁን፥ ሚቅንያን፥ በረኞችንም ዖቤድኤዶምንና ይዒኤልን አቆሙ።
19 ፤ መዘምራንም ኤማንና አሳፍ ኤታንም በናስ ጸናጽል ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር።
20 ፤ ዘካርያስ፥ ዓዝዔል፥ ሰሚራሞት፥ ይሒኤል፥ ዑኒ፥ ኤልያብ፥ መዕሤያ፥ በናያስ በመሰንቆ ምሥጢር ነገር ያዜሙ ነበር።
21 ፤ መቲትያ፥ ኤልፍሌሁ፥ ሚቅኒያ፥ ዖቤድኤዶም፥ ይዒኤል፥ ዓዛዝያ ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር።
22 ፤ የሌዋውያኑም አለቃ ክናንያ በዜማ ላይ ተሹሞ ነበር። ብልሃተኛ ነበረና ዜማ ያስተምራቸው ነበር።
23 ፤ በራክያና ሕልቃናም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ።
24 ፤ ካህናቱም ሰበንያ፥ ኢዮሳፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስ፥ አልዓዛር በእግዚአብሔር ታቦይ ፊት መለከት ይነፉ ነበር። ዖቤድኤዶምና ይሒያም ለታቦቱ በረኞች ነበሩ።
25 ፤ ዳዊትም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች፥ የሻለቆችም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢዳራ ቤት በደስታ ያመጡ ዘንድ ሄዱ።
26 ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያንን እግዚአብሔር በረዳቸው ጊዜ ሰባት በሬዎችና ሰባት አውራ በጎች ሰዉ።
27 ፤ ዳዊትም፥ ታቦቱንም የተሸከሙ ሌዋውያን ሁሉ፥ መዘምራኑም፥ የመዘምራኑም አለቃ ከናንያ የጥሩ በፍታ ቀሚስ ለብሰው ነበር፤ ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ነበረው።
28 ፤ እንዲሁ እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ።
29 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት ሲዘፍንና ሲጫወት አይታ በልቧ ናቀችው።