ኦሪት ዘኍልቍ. Chapter 23

1 ፤ በለዓምም ባላቅን። ሰባት መሠዊያ በዚህ ሥራልኝ፥ ሰባትም ወይፈን ሰባትም አውራ በግ በዚህ አዘጋጅልኝ አለው።
2 ፤ ባላቅም በለዓም እንደ ተናገረ አደረገ፤ ባላቅና በለዓምም በየመሠዊያው ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረጉ።
3 ፤ በለዓምም ባላቅን። በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ፥ እኔም እሄዳለሁ፤ ምናልባት እግዚአብሔር ሊገናኘኝ ይመጣል፤ እርሱም የሚገልጥልኝን እነግርሃለሁ አለው። ወደ ጉብታም ሄደ።
4 ፤ እግዚአብሔርም ከበለዓም ጋር ተገናኘ፤ እርሱም። ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጀሁ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረግሁ አለው።
5 ፤ እግዚአብሔርም ቃልን በበለዓም አፍ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው።
6 ፤ ወደ እርሱም ተመለሰ፥ እነሆም፥ እርሱና የሞዓብ አለቆች ሁሉ በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር።
7 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ።ባላቅ ከአራም አመጣኝ፥የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች፤ና፥ ያዕቆብን ርገምልኝ፤ና፥ እስራኤልን ተጣላልኝ ብሎ።
8 ፤ እግዚአብሔር ያልረገመውን እንዴት እረግማለሁ?
9 ፤ በአምቦች ራስ ላይ ሆኜ አየዋለሁ፥በኮረብቶችም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤እነሆ፥ ብቻውን የሚቀመጥ ሕዝብ ነው፥በአሕዛብም መካከል አይቈጠርም።
10 ፤ የያዕቆብን ትቢያ ማን ይቈጥራል?የእስራኤልስ እርቦ ማን ይቈጥራል?የጻድቃንን ሞት እኔ ልሙት፥ፍጻሜዬም እንደ እርሱ ፍጻሜ ትሁን።
11 ፤ ባላቅም በለዓምን። ያደረግህብኝ ምንድር ነው? ጠላቶቼን ትረግምልኝ ዘንድ ጠራሁህ፤ እነሆም፥ ፈጽመህ ባረክሃቸው አለው።
12 ፤ እርሱም መልሶ። በውኑ እግዚአብሔር በአፌ ያደረገውን እናገር ዘንድ አልጠነቀቅምን? አለው።
13 ፤ ባላቅም። በዚያ ሆነህ ታያቸው ዘንድ፥ እባክህ፥ ከእኔ ጋር ወደ ሌላ ቦታ ና ዳርቻቸውንም ብቻ ታያለህ፥ ሁሉን ግን አታይም፤ በዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ አለው።
14 ፤ ወደ ጾፊምም ሜዳ ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ ላይ ወሰደው፤ ሰባትም መሠዊያዎች ሠራ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈን አንድም አውራ በግ አሳረገ።
15 ፤ ባላቅንም። እኔ ወደዚያ ለመገናኘት ስሄድ በዚህ በመሥዋዕትህ ዘንድ ቆይ አለው።
16 ፤ እግዚአብሔርም በለዓምን ተገናኘ፥ ቃልንም በአፉ አድርጎ። ወደ ባላቅ ተመለስ፥ እንዲህም በል አለው።
17 ፤ ወደ እርሱም መጣ፥ እነሆም፥ እርሱ ከእርሱም ጋር የሞዓብ አለቆች በመሥዋዕቱ ዘንድ ቆመው ነበር፤ ባላቅም። እግዚአብሔር የተናገረው ምንድር ነው? አለው።
18 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ።ባላቅ ሆይ፥ ተነሣ፥ ስማ፤የሴፎር ልጅ ሆይ፥ አድምጠኝ፤
19 ፤ ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፥ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም።እርሱ ያለውን አያደርገውምን?የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?
20 ፤ እነሆ፥ ለመባረክ ትእዛዝን ተቀብያለሁ፤እርሱ ባርኮአል፥ እመልሰውም ዘንድ አልችልም።
21 ፤ በያዕቆብ ላይ ክፋትን አልተመለከተም፥በእስራኤልም ጠማምነትን አላየም፤አምላኩ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነው፥የንጉሥም እልልታ በመካከላቸው አለ።
22 ፤ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶአቸዋል፤ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው።
23 ፤ በያዕቆብ ላይ አስማት የለም፥በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም፤በጊዜው ስለ ያዕቆብና ስለ እስራኤል።እግዚአብሔር ምን አደረገ! ይባላል።
24 ፤ እነሆ፥ ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይቆማል፥እንደ አንበሳም ይነሣል፤ያደነውን አስኪበላ፥የገደለውንም ደሙን እስኪጠጣ አይተኛም።
25 ፤ ባላቅም በለዓምን። ከቶ አትርገማቸው፥ ከቶም አትባርካቸው አለው።
26 ፤ በለዓምም መልሶ ባላቅን። እግዚአብሔር የተናገረውን ሁሉ አደርጋለሁ ብዬ አልተናገርሁህምን? አለው።
27 ፤ ባላቅም በለዓምን። ና፥ ወደ ሌላ ስፍራ እወስድሃለሁ፤ ምናልባት በዚህ ሆነህ እነርሱን ትረግምልኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይወድዳል አለው።
28 ፤ ባላቅም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፌጎር ላይ በለዓምን ወሰደው።
29 ፤ በለዓምም ባላቅን። በዚህ ሰባት መሠዊያዎች ሥራልኝ፥ በዚህም ሰባት ወይፈን ሰባትም አውራ በግ አዘጋጅልኝ አለው።
30 ፤ ባላቅም በለዓም እንዳለው አደረገ፥ በየመሠዊያውም ላይ አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ አሳረገ።