ኦሪት ዘኍልቍ. Chapter 24

1 ፤ በለዓምም እግዚአብሔር እስራኤልን ይባርክ ዘንድ እንዲወድድ ባየ ጊዜ፥ አስቀድሞ ያደርግ የነበረውን አስማት ይሻ ዘንድ አልሄደም፤ ነገር ግን ወደ ምድረ በዳ ፊቱን አቀና።
2 ፤ በለዓምም ዓይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዱ ተቀምጦ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ መጣ።
3 ፤ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ።የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ዓይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤
4 ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል።
5 ፤ ያዕቆብ ሆይ፥ ድንኳኖችህ፥እስራኤል ሆይ ማደሪያዎችህ ምንኛ ያምራሉ!
6 ፤ እንደ ሸለቆች፥በወንዝ ዳር እንዳሉ አትክልቶች፥እግዚአብሔር እንደ ተከለው እሬትበውኃም ዳር እንዳሉ ዝግባዎች ተዘርግተዋል።
7 ፤ ከማድጋዎቹ ውኃ ይፈስሳል፥ዘሩም በብዙ ውኆች ይሆናል፥ንጉሡም ከአጋግ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፥ መንግሥቱም ይከበራል።
8 ፤ እግዚአብሔርም ከግብፅ አውጥቶታል፤ጕልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው፤ጠላቶቹን አሕዛብን ይበላል፥አጥንቶቻቸውንም ይሰባብራል፥በፍላጾቹም ይወጋቸዋል።
9 ፤ እንደ አንበሳ ዐርፎ ተኝቶአል፥እንደ እንስቲቱም አንበሳ ተጋድሞአል፤ማን ያስነሣዋል?የሚመርቅህ ሁሉ የተመረቀ ይሁን፥የሚረግምህም ሁሉ የተገመ ይሁን።
10 ፤ የባላቅም ቍጣ በበለዓም ላይ ነደደ፤ እጆቹንም አጨበጨበ፤ ባላቅም በለዓምን። ጠላቶቼን ትረግም ዘንድ ጠራሁህ፥ እነሆም፥ ሦስት ጊዜ ፈጽመህ መረቅሃቸው፤ አሁንም እንግዲህ ወደ ስፍራህ ሽሽ፤
11 ፤ እኔ አከብርህ ዘንድ ወድጄ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን፥ እነሆ፥ ክብርህን ከለከለ አለው።
13 ፤ በለዓምም ባላቅን አለው። ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ መልካሙን ወይም ክፉውን ከልቤ ለማድረግ የእግዚአብሔርን ቃል እተላለፍ ዘንድ አይቻለኝም፤ እግዚአብሔር የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ ብዬ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞች አልተናገርኋቸውምን?
14 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በኋለኛው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ።
15 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ።የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥ዓይኖቹም የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤
16 ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ፥የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥የወደቀው፥ ዓይኖቹም የተከፈቱለት እንዲህ ይላል።
17 ፤ አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥ከእስራኤል በትር ይነሣል፥የሞዓብንም ማዕዘኖች ይመታል፥የሤትንም ልጆች ያጠፋል።
18 ፤ ኤዶምያስም ርስቱ ይሆናል፥ጠላቱ ሴይር ደግሞ ርስቱ ይሆናል፤እስራኤልም በኃይል ያደርጋል።
19 ፤ ከያዕቆብም የሚወጣ ገዥ ይሆናል፥ከከተማውም የቀሩትን ያጠፋል።
20 ፤ አማሌቅንም አይቶ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ።አማሌቅ የአሕዛብ አለቃ ነበረ፤ፍጻሜው ግን ወደ ጥፋት ይመጣል።
21 ፤ ቄናውያንንም አይቶ ምሳሌውን ይምስል ጀመር፥ እንዲህም አለ።ማደሪያህ የጸና ነው፥ጎጆህም በአምባ ላይ ተሠርቶአል፤
22 ፤ ነገር ግን አሦር እስኪማርክህ ድረስ ቄናዊው ለጥፋት ይሆናል።
23 ፤ ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ።እግዚአብሔር ይህን ሲያደርግአወይ! ማን በሕይወት ይኖራል?
24 ፤ ከኪቲም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፥አሦርንም ያስጨንቃሉ፥ዔቦርንም ያስጨንቃሉ፤እርሱም ደግሞ ወደ ጥፋት ይመጣል።
25 ፤ በለዓምም ተነሣ፥ ተመልሶም ወደ ስፍራው ሄደ፤ ባላቅም ደግሞ መንገዱን ሄደ።