ኦሪት ዘኍልቍ. Chapter 32

1 ፤ የሮቤልና የጋድ ልጆችም እጅግ ብዙ እንስሶች ነበሩአቸው፤ እነሆም፥ የኢያዜር ምድርና የገለዓድ ምድር ለእንስሶች የተመቸ ስፍራ እንደ ነበረ ባዩ ጊዜ፥
2 ፤ የጋድና የሮቤል ልጆች መጥተው ሙሴንና ካህኑን አልዓዛርን የማኅበሩንም አለቆች እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው።
3 ፤4፤ እግዚአብሔር በእስራኤል ማኅበር ፊት የመታው ምድር፥ አጣሮት፥ ዲቦን፥ ኢያዜር፥ ነምራ፥ ሐሴቦን፥ ኤልያሊ፥ ሴባማ፥ ናባው፥ ባያን፥ ለእንስሶች የተመቸ ምድር ነው፤ ለእኛም ለባሪያዎችህ እንስሶች አሉን።
5 ፤ እኛስ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝተን እንደ ሆነ ይህን ምድር ለባሪያዎችህ ርስት አድርገህ ስጠን፤ ወደ ዮርዳኖስም ማዶ አታሻግረን።
6 ፤ ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች አላቸው። ወንድሞቻችሁ ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ በዚህ ትቀመጣላችሁን?
7 ፤ እግዚአብሔር ወደሚሰጣቸው ምድር እንዳይሻገሩ የእስራኤልን ልጆች ልብ ለምን ታደክማላችሁ?
8 ፤ ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በሰደድኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ እንዲህ አደረጉ።
9 ፤ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ በሄዱ ጊዜ፥ ምድሪቱንም ባዩ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ የእስራኤልን ልጆች ልብ አደከሙ።
10 ፤ በዚያም ቀን የእግዚአብሔር ቍጣ ነደደ፥
12 ፤ እርሱም። በእውነት እግዚአብሔርን ፈጽመው ከተከተሉ ከእነዚህ ከቄኔዛዊው ከዮፎኔ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር፥ ከግብፅ የወጡት ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት ሰዎች እኔን ፈጽመው አልተከተሉምና ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጥ ዘንድ የማልሁበትን ምድር አያዩም ብሎ ማለ።
13 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ጸና፥ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ያደረገ ትውልድ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ አርባ ዓመት በምድረ በዳ ውስጥ አቅበዘበዛቸው።
14 ፤ እነሆም፥ የእግዚአብሔርን መዓት በእስራኤል ላይ አብዝታችሁ ትጨምሩ ዘንድ እናንተ የኃጢአተኞች ትውልድ በአባቶቻችሁ ፋንታ ቆማችኋል።
15 ፤ እርሱን ከመከተል ብትመለሱ እርሱ ሕዝቡን በምድረ በዳ ደግሞ ይተዋል፤ ይህንንም ሕዝብ ሁሉ ታጠፋላችሁ።
16 ፤ ወደ እርሱም ቀርበው አሉት። በዚህ ለእንስሶቻችን በረቶች ለልጆቻችንም ከተሞች እንሠራለን፤
17 ፤ እኛ ግን ለጦርነት ተዘጋጅተን ወደ ስፍራቸው እስክናገባቸው ድረስ በእስራኤል ልጆች ፊት እንሄዳለን፤ በዚህም ምድር ስላሉ ሰዎች ልጆቻችን በተመሸጉ ከተሞች ይቀመጣሉ።
18 ፤ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ርስታቸውን እስኪወርሱ ድረስ ወደ ቤቶቻችን አንመለስም፤
19 ፤ ከዮርዳኖስ ወዲህ ወደ ምሥራቅ ርስታችን ደርሶናልና እኛ ከዮርዳኖስ ማዶ ወደዚያ ከእነርሱ ጋር ርስት አንወርስም።
20 ፤ ሙሴም አላቸው። ይህንስ ነገር ብታደርጉ፥ ተዘጋጅታችሁም በእግዚአብሔር ፊት ወደ ሰልፍ ብትሄዱ፥
21 ፤ እርሱም ጠላቶቹን ከፊቱ እስኪያሳድድ ድረስ ምድሪቱም በእግዚአብሔር ፊት ድል እስክትሆን ድረስ ከእናንተ ሰው ሁሉ ጋሻ ጦሩን ይዞ በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገር፥
22 ፤ ከዚያ በኋላ ትመለሳላችሁ፥ በእግዚአብሔርም ፊት በእስራኤል ዘንድ ንጹሐን ትሆናላችሁ፤ ይህች ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ርስት ትሆንላችኋለች።
23 ፤ እናንተ ግን እንዲህ ባታደርጉ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ፤ ኃጢአታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ።
24 ፤ ለልጆቻችሁ ከተሞች፥ ለበጎቻችሁም በረቶች ሥሩ፤ ከአፋችሁም የወጣውን ነገር አድርጉ።
25 ፤ የጋድና የሮቤልም ልጆች ሙሴን እንዲህ ብለው ተናገሩት። እኛ ባሪያዎችህ ጌታችን እንዳዘዘ እናደርጋለን።
26 ፤ ልጆቻችን፥ ሚስቶቻችንም፥ መንጎቻችንም፥ እንስሶቻችንም ሁሉ በዚያ በገለዓድ ከተሞች ይሆናሉ፤
27 ፤ እኛ ባሪያዎችህ ግን ሁላችን ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ጌታችን እንደ ተናገረ ወደ ጦርነት እንሄዳለን።
28 ፤ ሙሴም ካህኑን አልዓዛርን የነዌንም ልጅ ኢያሱን የእስራኤልንም ልጆች ነገድ አለቆች ስለ እነርሱ አዘዘ።
29 ፤ ሙሴም። የጋድና የሮቤል ልጆች ሁላቸው ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ዮርዳኖስን ቢሻገሩ፥ ምድሪቱንም ድል ብትነሡ፥ የገለዓድን ምድር ርስት አድርጋችሁ ትሰጡአቸዋላችሁ።
30 ፤ ጋሻ ጦራቸውን ይዘው ከእናንተ ጋር ባይሻገሩ ግን በከነዓን ምድር በእናንተ መካከል ርስታቸውን ይወርሳሉ አላቸው።
31 ፤ የጋድና የሮቤልም ልጆች መልሰው። እግዚአብሔር ለእኛ ለባሪያዎችህ እንደ ተናገረ እንዲሁ እናደርጋለን።
32 ፤ ጋሻ ጦራችንን ይዘን በእግዚአብሔር ፊት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፥ ከዮርዳኖስም ማዶ ከወዲሁ የወረስነው ርስት ይሆንልናል አሉት።
33 ፤ ሙሴም ለጋድና ለሮቤል ልጆች ለዮሴፍም ልጅ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ፥ የአሞራውያንን ንጉሥ የሴዎንን ግዛት የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ግዛት፥ ምድሪቱንና በዙሪያዋ ያሉትን ከተሞች ሰጣቸው።
34 ፤ የጋድም ልጆች ዲቦንን፥ አጣሮትን፥ አሮዔርን፥
35 ፤ ዓጥሮትሽፋንን፥ ኢያዜርን፥ ዮግብሃን፥
36 ፤ ቤትነምራን፥ ቤትሃራንን የተመሸጉ ከተሞች አድርገው ሠሩ፤ የበጎች በረቶችንም ሠሩ።
37 ፤ የሮቤልም ልጆች ሐሴቦንን፥ ኤልያሊን፥
38 ፤ ቂርያታይምን፥ ስማቸውም የተለወጠውን ናባውን፥ በኣልሜዎንን፥ ሴባማን ሠሩ፤ እነዚህንም የሠሩአቸውን ከተሞች በሌላ ስም ጠሩአቸው።
39 ፤ የምናሴም ልጅ የማኪር ልጆች ወደ ገለዓድ ሄዱ፥ ወሰዱአትም፥ በእርስዋም የነበሩትን አሞራውያንን አሳደዱ።
40 ፤ ሙሴም ለምናሴ ልጅ ለማኪር ገለዓድን ሰጠ፤ በእርስዋም ተቀመጠ።
41 ፤ የምናሴም ልጅ ኢያዕር ሄዶ መንደሮችዋን ወሰደ፥ የኢያዕርም መንደሮች ብሎ ጠራቸው።
42 ፤ ኖባህም ሄደ ቄናትንም መንደሮችዋንም ወሰደ፥ በስሙም ኖባህ ብሎ ጠራቸው።