የማርቆስ ወንጌል. Chapter 10

1 ከዚያም ተነሥቶ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ ደግሞም ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ እንደ ልማዱም ደግሞ ያስተምራቸው ነበር።
2 ፈሪሳውያንም ቀርበው። ሰው ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት።
3 እርሱ ግን መልሶ። ሙሴ ምን አዘዛችሁ? አላቸው።
4 እነርሱም። ሙሴስ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቀደ አሉ።
5 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ይህችን ትእዛዝ ጻፈላችሁ።
6 ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤
7 ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥
8 ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም።
9 እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።
10 በቤትም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር ጠየቁት።
11 እርሱም። ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤
12 እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች አላቸው።
13 እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው።
14 ኢየሱስ ግን አይቶ ተቈጣና። ሕፃናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉ አትከልክሉአቸው፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና።
15 እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበላት ሁሉ ከቶ አይገባባትም አላቸው።
16 አቀፋቸውም እጁንም ጭኖ ባረካቸው።
17 እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና። ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው።
18 ኢየሱስም። ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም።
19 ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው።
20 እርሱም መልሶ። መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው።
21 ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና። አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው።
22 ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ።
23 ኢየሱስም ዘወር ብሎ አይቶ ደቀ መዛሙርቱን። ገንዘብ ላላቸው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ይሆናል አላቸው።
24 ደቀ መዛሙርቱም እነዚህን ቃሎች አደነቁ። ኢየሱስም ደግሞ መልሶ። ልጆች ሆይ፥ በገንዘብ ለሚታመኑ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንዴት ጭንቅ ነው።
25 ባለ ጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል አላቸው።
26 እነርሱም ያለ መጠን ተገረሙና እርስ በርሳቸው። እንግዲያ ማን ሊድን ይችላል? ተባባሉ።
27 ኢየሱስም ተመለከታቸውና። ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላልና አለ።
28 ጴጥሮስም። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ ይለው ጀመር።
29 ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥
30 አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።
31 ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።
32 ወደ ኢየሩሳሌምም ሊወጡ በመንገድ ነበሩ፥ ኢየሱስም ይቀድማቸው ነበርና ተደነቁ፤ የተከተሉትም ይፈሩ ነበር። ደግሞም አሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ አቅርቦ ይደርስበት ዘንድ ያለውን ይነግራቸው ጀመር።
33 እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፥ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል፥
34 ይዘብቱበትማል ይተፉበትማል ይገርፉትማል ይገድሉትማል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው።
35 የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስም ወደ እርሱ ቀርበው። መምህር ሆይ፥ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን አሉት።
36 እርሱም። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው።
37 እነርሱም። በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራህ መቀመጥን ስጠን አሉት።
38 ኢየሱስ ግን። የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፥ እኔ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አላቸው።
39 እነርሱም። እንችላለን አሉት። ኢየሱስም። እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፥ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤
40 በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ የምሰጥ እኔ አይደለሁም አላቸው።
41 አሥሩም ሰምተው በያዕቆብና በዮሐንስ ይቈጡ ጀመር።
42 ኢየሱስም ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው። የአሕዛብ አለቆች ተብሎ የምታስቡት እንዲገዙአቸው ታላላቆቻቸውም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ።
43 በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥
44 ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤
45 እንዲሁ የሰው ልጅም ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።
46 ወደ ኢያሪኮም መጡ። ከደቀ መዛሙርቱና ከብዙ ሕዝብ ጋር ከኢያሪኮ ሲወጣ የጤሜዎስ ልጅ ዕውሩ በርጤሜዎስ እየለመነ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ነበር።
47 የናዝሬቱ ኢየሱስም እንደ ሆነ በሰማ ጊዜ። የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ማረኝ እያለ ይጮኽ ጀመር።
48 ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረኝ እያለ አብዝቶ ጮኸ።
49 ኢየሱስም ቆመና። ጥሩት አለ። ዕውሩንም። አይዞህ፥ ተነሣ፥ ይጠራሃል ብለው ጠሩት።
50 እርሱም እየዘለለ ተነሣና ልብሱን ጥሎ ወደ ኢየሱስ መጣ።
51 ኢየሱስም መልሶ። ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? አለው። ዕውሩም። መምህር ሆይ፥ አይ ዘንድ አለው።
52 ኢየሱስም። ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ወዲያውም አየ በመንገድም ተከተለው።