መጽሐፈ መሣፍንት. Chapter 2

1 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ። እኔ ከግብፅ አውጥቻችኋለሁ፥ ለአባቶቻችሁም ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ፤ እኔም። ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘላለም አላፈርስም፤
2 ፤ እናንተም መሠዊያቸውን አፍርሱ እንጂ በዚህች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም፤
3 ፤ ይህንስ ለምን አደረጋችሁ? ስለዚህም። ከፊታችሁ አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ያስጨንቋችኋል፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል አልሁ።
4 ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ።
5 ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ቦኪም ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለእግዚአብሔር ሠዉ።
6 ፤ ኢያሱም ሕዝቡን ባሰናበተ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ምድሪቱን ሊወርሱ ወደ እየርስታቸው ሄዱ።
7 ፤ ኢያሱም በነበረበት ዘመን ሁሉ፥ ለእስራኤልም ያደረገውን ታላቁን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባዩት፥ ከኢያሱ በኋላ በነበሩ ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለኩ።
8 ፤ የእግዚአብሔርም ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ አሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ።
9 ፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሔሬስ ቀበሩት።
10 ፤ ትውልድ ሁሉ ደግሞ ወደ አባቶቻቸው ተከማቹ፤ ከእነዚያም በኋላ እግዚአብሔርን ለእስራኤልም ያደረገውን ሥራ ያላወቀ ሌላ ትውልድ ተነሣ።
11 ፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነ ነገር አደረጉ፥ በኣሊምንም አመለኩ።
12 ፤ ከግብፅ ምድርም ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፥ በዙሪያቸውም ካሉት ከአሕዛብ አማልክት ሌሎችን አማልክት ተከተሉ፥ ሰገዱላቸውም፤ እግዚአብሔርንም አስቈጡ።
13 ፤ እግዚአብሔርንም ትተው በኣልንና አስታሮትን አመለኩ።
14 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ ወደ ማረኩአቸውም ማራኪዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸውም ባሉት በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ጠላቶቻቸውንም ከዚያ ወዲያ ሊቋቋሙ አልቻሉም።
15 ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ እንደማለ፥ ወደ ወጡበት ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበረች፤ እጅግም ተጨነቁ።
16 ፤ እግዚአብሔርም መሳፍንትን አስነሣላቸው፥ ከሚማርኩአቸውም እጅ አዳኑአቸው።
17 ፤ ሌሎች አማልክትን ተከትለው አመነዘሩ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንቶቻቸውን አልሰሙም፤ አባቶቻቸውም ይሄዱበት ከነበረ መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ አባቶቻቸው ለእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ታዘዙ እንዲሁ አላደረጉም።
18 ፤ እግዚአብሔርም መሳፍንትን ባስነሣላቸው ጊዜ እግዚአብሔር ከመስፍኑ ጋር ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስለሚጋፉአቸውና ስለሚያስጨንቋቸው በጩኸታቸው ያዝን ነበርና በመስፍኑ ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ አዳናቸው።
19 ፤ መስፍኑ ግን ከሞተ በኋላ ይመለሱ ነበር፥ ሌሎችንም አማልክት በመከተላቸው እነርሱንም በማምለካቸውና ለእነርሱ በመስገዳቸው አባቶቻቸው አድርገውት ከነበረው የከፋ ያደርጉ ነበር፤ የእልከኝነታቸውን መንገድና ሥራቸውን አልተዉም ነበር።
20 ፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ እንዲህም አለ። ይህ ሕዝብ ለአባቶቻቸው ያዘዝሁትን ቃል ኪዳን ስለ ተላለፉ፥ ድምፄንም ስላልሰሙ አባቶቻቸውም እንደ ጠበቁ፥
22 ፤ ይሄዱባት ዘንድ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ወይም አይጠብቁ እንደ ሆነ እስራኤልን እፈትንባቸው ዘንድ፥ ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው አሕዛብ አንዱን ሰው እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ ከፊታቸው አላወጣም።
23 ፤ እግዚአብሔርም እነዚህን አሕዛብ አስቀረ፥ ፈጥኖም አላወጣቸውም፥ በኢያሱም እጅ አሳልፎ አልሰጣቸውም።