መጽሐፈ መሣፍንት. Chapter 5
1 ፤ በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ እንዲህ ብለው ተቀኙ።
2 ፤ በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥እግዚአብሔርን አመስግኑ።
3 ፤ ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፤መኳንንት ሆይ፥ አድምጡ፤እኔ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ።
4 ፤ አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፤ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ።
5 ፤ ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ቀለጡ፥ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ።
6 ፤ በዓናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፥በኢያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፤መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር።
7 ፤ አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም።
8 ፤ አዲሶች አማልክትን መረጡ፤በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፤በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም።
9 ፤ ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፤እግዚአብሔርን አመስግኑ።
10 ፤ በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥በወላንሳ ላይ የምትቀመጡ፥በመንገድም የምትሄዱ፥ ተናገሩ።
11 ፤ በማጠጫው መካከል ካሉት ከቀስተኞች ጩኸት ርቀው፥በዚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ፥በእስራኤል ላይ የግዛቱን ጽድቅ ይጫወታሉ፤ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ በሮች ወረዱ።
12 ፤ ንቂ፥ ንቂ፥ ዲቦራ ሆይ፤ንቂ፥ ንቂ፥ ቅኔውን ተቀኚ፤ባርቅ ሆይ፥ ተነሣ፤የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፥ ምርኮህን ማርክ።
13 ፤ በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኃያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፤እግዚአብሔርም ስለ እኔ በኃያላን ላይ ወረደ።
14 ፤ በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥ብንያም ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፤አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ።
15 ፤ የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤ይሳኮርም እንደ ባርቅ ነበረ፤ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኰሉ፤በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ።
16 ፤ መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማትበበጎች ጕረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ?በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ።
17 ፤ ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፤ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ?አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ።
18 ፤ ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፥ንፍታሌምም በአገሩ ኮረብታ ላይ ነው።
19 ፤ ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፤በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክየከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፤የብር ዘረፋም አልወሰዱም።
20 ፤ ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ።
21 ፤ ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው።ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ።
22 ፤ ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣየፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ።
23 ፤ የእግዚአብሔር መልአክ። ሜሮዝን እርገሙ፤እግዚአብሔርን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምናየተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ።
24 ፤ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔልከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፤በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን።
25 ፤ ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፤በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት።
26 ፤ እጅዋን ወደ ካስማ፥ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፤በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፤ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም።
27 ፤ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፤በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፤በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ።
28 ፤ ከመስኮት ሆና ተመለከተች፤የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ።ስለ ምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ?ስለ ምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች።
29 ፤ ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፤እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች።
30 ፤ ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን?ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፤ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጕርጕር ልብስ።
31 ፤ አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።