መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ. Chapter 10
1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ኢያሱ ጋይን እንደ ያዘ ፈጽሞም እንዳጠፋት፥ በኢያሪኮና በንጉሥዋም ያደረገውን እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ እንዳደረገ፥ የገባዖንም ሰዎች ከእስራኤል ጋር ሰላም እንዳደረጉ በመካከላቸውም እንደ ሆኑ በሰማ ጊዜ፥
2 ፤ ገባዖን ከመንግሥታት ከተሞች እንደ አንዲቱ ታላቅ ከተማ ስለ ሆነች፥ ከጋይም ስለ በለጠች፥ ሰዎችዋም ሁሉ ኃያላን ስለ ነበሩ፥ እጅግ ፈራ።
3 ፤ ስለዚህም የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ወደ ኬብሮን ንጉሥ ወደ ሆሃም፥ ወደ የርሙት ንጉሥም ወደ ጲርአም፥ ወደ ለኪሶ ንጉሥም ወደ ያፊዓ፥ ወደ አዶላም ንጉሥም ወደ ዳቤር ልኮ። ወደ እኔ ውጡ፥
4 ፤ ከኢያሱና ከእስራኤልም ልጆች ጋር ሰላም አድርገዋልና ገባዖንን ለመምታት አግዙኝ አለ።
5 ፤ አምስቱም የአሞራውያን ነገሥታት፥ የኢየሩሳሌም ንጉሥ፥ የኬብሮን ንጉሥ፥ የየርሙት ንጉሥ፥ የለኪሶ ንጉሥ፥ የአዶላም ንጉሥ፥ ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ጋር ተሰብስበው ወጡ፥ ከገባዖንም ጋር ሊጋጠሙ ከበቡአት።
6 ፤ የገባዖንም ሰዎች ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ልከው። ባሪያዎችህን ለመርዳት እጅህን አትመልስ፤ በተራራማው አገር የሚኖሩ የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበውብናልና ፈጥነህ ወደ እኛ ውጣ አድነንም እርዳንም አሉት።
7 ፤ ኢያሱም ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰልፈኞች ሁሉ ጽኑዓን ኃያላኑም ሁሉ ከጌልገላ ወጡ።
8 ፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን። በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁና አትፍራቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው የሚቋቋምህ የለም አለው።
9 ፤ ኢያሱም ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሦ በድንገት መጣባቸው።
10 ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ፊት አስደነገጣቸው፤ በገባዖንም ታላቅ መምታት መታቸው፥ በቤትሖሮንም ዐቀበት በመንገድ አሳደዳቸው፥ እስከ ዓዜቃና እስከ መቄዳ ድረስ መታቸው።
11 ፤ ከእስራኤልም ልጆች ፊት እየሸሹ በቤትሖሮን ቍልቍለት ሲወርዱ፥ ወደ ዓዜቃ እስኪደርሱ ድረስ እግዚአብሔር ከሰማይ ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸውና ሞቱ፤ የእስራኤል ልጆች በሰይፍ ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት በለጡ።
12 ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል ልጆች እጅ አሞራውያንን አሳልፎ በሰጠ ቀን ኢያሱ እግዚአብሔርን ተናገረ፤ በእስራኤልም ፊት እንዲህ አለ። በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፥ በኤሎንም ሸለቆ ጨረቃ፤
13 ፤ ሕዝቡም ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፥ ጨረቃም ዘገየ። ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ፀሐይም በሰማይ መካከል ዘገየ፥ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል ለመግባት አልቸኰለም።
14 ፤ እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም።
15 ፤ ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ሰፈራቸው ወደ ጌልገላ ተመለሱ።
16 ፤ እነዚህም አምስት ነገሥታት ሸሽተው በመቄዳ ዋሻ ተሸሸጉ።
17 ፤ ለኢያሱም። አምስቱ ነገሥታት በመቄዳ ዋሻ ተሸሽገው ተገኙ ብለው ነገሩት።
18 ፤ ኢያሱም እንዲህ አለ። ወደ ዋሻው አፍ ታላላቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ፥ ይጠብቁአቸው ዘንድ ሰዎችን በዚያ አኑሩ፤
19 ፤ እናንተ ግን አትዘግዩ፥ ጠላቶቻችሁንም አባርሩአቸው፥ በኋላም ያሉትን ግደሉ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ወደ ከተሞቻቸው እንዳይገቡ ከልክሉአቸው አለ።
20 ፤ እስኪጠፉም ድረስ ኢያሱና የእስራኤል ልጆች በታላቅ መምታት መምታታቸውን በፈጸሙ ጊዜ፥ ከእነርሱም ያመለጡት ወደ ተመሸገ ከተማ በገቡ ጊዜ፥
21 ፤ ሕዝብ ሁሉ ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ መቄዳ በደኅና ተመለሱ፤ በእስራኤል ልጆች ላይ ምላሱን ማንቀሳቀስ የደፈረ ማንም ሰው የለም።
22 ፤ ኢያሱም። የዋሻውን አፍ ክፈቱ፥ እነዚያንም አምስት ነገሥታት ከዋሻው ወደ እኔ አውጡአቸው አለ።
23 ፤ እንዲህም አደረጉ፤ አምስቱንም ነገሥታት፥ የኢየሩሳሌምን ንጉሥ የኬብሮንንም ንጉሥ የየርሙትንም ንጉሥ የለኪሶንም ንጉሥ የኦዶላምንም ንጉሥ፥ ከዋሻው ወደ እርሱ አወጡአቸው።
24 ፤ እነዚያንም ነገሥታት ወደ ኢያሱ ባወጡአቸው ጊዜ ኢያሱ የእስራኤልን ሰዎች ሁሉ ጠራ፥ ከእርሱም ጋር የሄዱትን የሰልፈኞች አለቆች። ቅረቡ፥ በእነዚህም ነገሥታት አንገት ላይ እግራችሁን አኑሩ አላቸው። ቀረቡም በአንገታቸውም ላይ እግራቸውን አኖሩ።
25 ፤ ኢያሱም። እግዚአብሔር በምትወጉአቸው በጠላቶቻችሁ ሁሉ ላይ እንዲሁ ያደርጋልና አትፍሩ፥ አትደንግጡ፤ ጽኑ፥ አይዞአችሁ አላቸው።
26 ፤ ከዚህም በኋላ መትተው ገደሉአቸው፥ በአምስቱም ዛፎች ላይ ሰቀሉአቸው፤ እስከ ማታም ድረስ በዛፎቹ ተሰቅለው ቈዩ።
27 ፤ ፀሐይም ልትገባ በቀረበች ጊዜ ኢያሱ አዘዘ፥ ከዛፎችም አወረዱአቸው፥ ተሸሽገውም በነበሩበት ዋሻ ጣሉአቸው፥ እስከ ዛሬም ድረስ በዋሻው አፍ ታላላቅ ድንጋይ ተደርጎአል።
28 ፤ በዚያም ቀን ኢያሱ መቄዳን ያዛት፥ እርስዋንና ንጉሥዋንም በሰይፍ ስለት መታ፤ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽሞ አጠፋቸው፥ ከእነርሱም አንዱን ስንኳ አላስቀረም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ እንዳደረገ በመቄዳ ንጉሥ አደረገ።
29 ፤ ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከመቄዳ ወደ ልብና አለፉ፥ ልብናንም ወጉ።
30 ፤ እግዚአብሔርም እርስዋንና ንጉሥዋን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፤ እርስዋንም በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መታ፥ በእርስዋም አንዱን ስንኳ አላስቀረም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ እንዳደረገው በልብና ንጉሥ አደረገ።
31 ፤ ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከልብና ወደ ለኪሶ አለፉ፥ ከበቡአትም፥ ወጉአትም።
32 ፤ እግዚአብሔርም ለኪሶን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣት፥ በሁለተኛውም ቀን ያዙአት፤ በልብናም እንዳደረጉት ሁሉ፥ እርስዋን በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱአቸው።
33 ፤ በዚያን ጊዜም የጌዝር ንጉሥ ሆራም ለኪሶን ለመርዳት ወጣ፤ ኢያሱም አንድ ስንኳ ሳይቀር እርሱንና ሕዝቡን መታ።
34 ፤ ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከለኪሶ ወደ ኦዶላም አለፉ፥ ከበቡአትም፥ ወጉአትም፤
35 ፤ በዚያም ቀን ያዙአት፥ በሰይፍም ስለት መቱአት፤ በለኪሶም እንዳደረገው ሁሉ፥ በእርስዋ ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በዚያ ቀን ፈጽሞ አጠፋ።
36 ፤ ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከኦዶላም ወደ ኬብሮን ወጡ፥ ወጉአትም፥ ያዙአትም፤
37 ፤ እርስዋንም ንጉሥዋንም ከተሞችዋንም ሁሉ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱ፤ በኦዶላም እንዳደረገው ሁሉ ማንንም አላስቀረም፤ እርስዋንም በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ።
38 ፤ ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ዳቤር ተመለሱ፥ ወጉአትም፥
39 ፤ እርስዋንም ንጉሥዋንም ከተሞችዋንም ያዙ፤ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፥ በእነርሱም ውስጥ ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽመው አጠፉ፤ ማንንም አላስቀረም፤ በኬብሮን፥ ደግሞ በልብናና በንጉሥዋ እንዳደረገው እንዲሁ በዳቤርና በንጉሥዋ አደረገ።
40 ፤ እንዲሁም ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ተራራማውን አገር ደቡቡንም ቈላውንም ቍልቍለቱንም ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ መታ፤ ማንንም አላስቀረም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዳዘዘውም ነፍስ ያለበትን ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ።
41 ፤ ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ እስከ ጋዛ ድረስ የጎሶምንም ምድር ሁሉ እስከ ገባዖን ድረስ መታ።
42 ፤ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ለእስራኤል ስለ ተዋጋላቸው ኢያሱ እነዚህን ነገሥታት ሁሉ ምድራቸውንም በአንድ ጊዜ ያዘ።
43 ፤ ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ሰፈሩ ወደ ጌልገላ ተመለሱ። a