መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ. Chapter 11
1 ፤ እንዲህም ሆነ፤ የአሶር ንጉሥ ኢያቢስ ይህን በሰማ ጊዜ ወደ ማዶን ንጉሥ ወደ ዮባብ፥ ወደ ሺምሮንም ንጉሥ፥ ወደ አዚፍም ንጉሥ፥
2 ፤ በሰሜንም በተራራማው አገር፥ በኪኔሬትም ደቡብ በዓረባ፥ በቈላውም፥ በምዕራብም በኩል ባለ በዶር ኮረብታ ወደ ነበሩ ነገሥታት፥
3 ፤ በምሥራቅና በምዕራብም ወዳለው ወደ ከነዓናዊው፥ ወደ አሞራዊውም፥ ወደ ኬጢያዊውም፥ ወደ ፌርዛዊውም፥ በተራራማውም አገር ወዳለው ወደ ኢያቡሳዊው፥ ከአርሞንዔምም በታች በምጽጳ ወዳለው ወደ ኤዊያዊው ላከ።
4 ፤ እነዚህም ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ከእጅግም ብዙ ፈረሰኞችና ሠረገሎች ጋር ወጡ፤ በባሕር ዳርም እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበረ።
5 ፤ እነዚህም ነገሥታት ሁሉ ተሰብስበው እስራኤልን ለመውጋት መጥተው በማሮን ውኃ አጠገብ አንድ ሆነው ሰፈሩ።
6 ፤ እግዚአብሔርም ኢያሱን። ነገ በዚህ ጊዜ ሁሉን እንደ ሞቱ አድርጌ በእስራኤል እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና አትፍራቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ትቈርጣለህ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት ታቃጥላለህ አለው።
7 ፤ ኢያሱም ከሰልፈኞቹ ሁሉ ጋር በድንገት ወደ ማሮን ውኃ መጣባቸው፥ ወደቀባቸውም።
8 ፤ እግዚአብሔርም በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ መቱአቸውም፥ ወደ ታላቂቱም ሲዶና፥ ወደ ማሴሮንም፥ በምሥራቅም በኩል ወዳለው ወደ ምጽጳ ሸለቆ አሳደዱአቸው፤ ማንንም ሳያስቀሩ መቱአቸው።
9 ፤ ኢያሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገባቸው፤ የፈረሶቻቸውንም ቋንጃ ቈረጠ፥ ሰረገሎቻቸውንም በእሳት አቃጠለ።
10 ፤ በዚያን ጊዜም ኢያሱ ተመልሶ አሶርን ያዘ፥ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ አሶርም አስቀድሞ የእነዚህ መንግሥታት ዋና ከተማ ነበረች።
11 ፤ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት ገደሉ፥ ፈጽመውም አጠፉአቸው፤ እስትንፋስ ያለውንም አላስቀሩም፤ አሶርንም በእሳት አቃጠላት።
12 ፤ የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ እንዳዘዘው፥ ኢያሱ የእነዚህን ነገሥታት ከተሞች ሁሉ፥ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ያዘ፥ በሰይፍም ስለት መታቸው፥ ፈጽሞም አጠፋቸው።
13 ፤ እስራኤልም በኮረብቶቹ ላይ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ አላቃጠሉም፤ ነገር ግን እስራኤል አሶርን ብቻ አቃጠሉአት።
14 ፤ የእስራኤልም ልጆች የእነዚህን ከተሞች ምርኮ ሁሉ ከብቶቹንም ለራሳቸው ዘረፉ፤ ሰዎቹን ሁሉ ግን እስኪጠፉ ድረስ በሰይፍ ስለት መቱአቸው፥ እስትንፋስ ያለውንም ሁሉ አላስቀሩም።
15 ፤ እግዚአብሔርም ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ሙሴ ኢያሱን አዝዞት ነበር፥ ኢያሱም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ካዘዘው ሁሉ ምንም አላስቀረም።
16 ፤ ኢያሱም ያን ምድር ሁሉ፥ ተራራማውን፥ ደቡቡንም ሁሉ፥ የጎሶምንም ምድር ሁሉ፥ ቈላውንም፥ ዓረባንም፥ የእስራኤልንም ተራራማውንና ቈላውን ያዘ፥
17 ፤ እስከ ሴይርም ከሚያወጣው ወና ከሆነው ተራራ ጀምሮ ከአርሞንዔም ተራራ በታች በሊባኖስም ሸለቆ ውስጥ እስካለው እስከ በኣልጋድ ድረስ፤ ነገሥታቶቻቸውንም ሁሉ ይዞ መታቸው፥ ገደላቸውም።
18 ፤ ኢያሱም ብዙ ዘመን ከእነዚህ ነገሥታት ሁሉ ጋር ይዋጋ ነበር።
19 ፤ በገባዖን ከሚኖሩ ከኤዊያውያን በቀር ከእስራኤል ልጆች ጋር ዕርቅ ያደረገች አንዲት ከተማ አልነበረችም፤ ሁሉን በሰልፍ ያዙ።
20 ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ፥ ያጠፉአቸው ዘንድ ሞገስንም እንዳያገኙ ፈጽመውም እንዲያጠፉአቸው፥ ከእስራኤል ጋር ይጋጠሙ ዘንድ ልባቸውን እንዲያደነድኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነ።
21 ፤ በዚያን ጊዜም ኢያሱ መጣ፥ ከተራራማውም አገር ከኬብሮንም ከዳቤርም ከአናብም ከእስራኤልም ተራራማ ሁሉ ከይሁዳም ተራራማ ሁሉ የዔናቅን ልጆች ገደለ፤ ኢያሱም ከከተሞቻቸው ጋር ፈጽሞ አጠፋቸው።
22 ፤ በጋዛ በጌትም በአዛጦንም ጥቂቶች ቀሩ እንጂ በእስራኤል ልጆች ምድር ከዔናቅ ልጆች ማንም አልቀረም።
23 ፤ እግዚአብሔርም ለሙሴ እንደ ነገረው ሁሉ ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ ያዘ፤ ኢያሱም ለእስራኤል እንደ ክፍላቸውና እንደ ነገዳቸው ርስት አድርጎ ምድሪቱን ሰጣቸው፤ ምድሪቱም ከሰልፍ ዐረፈች።