መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 22

1 ፤ ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ በውኑ ሰው እግዚአብሔርን ይጠቅመዋልን?በእውነት ጥበበኛ ሰው ራሱን ይጠቅማል።
3 ፤ ጻድቅ መሆንህስ ሁሉን የሚችለውን አምላክ ደስ ያሰኘዋልን?መንገድህን ማቅናትህስ ይጠቅመዋልን?
4 ፤ እርሱንስ ስለ ፈራህ ይዘልፍሃልን?ወደ ፍርድስ ከአንተ ጋር ይገባልን?
5 ፤ ክፋትህስ የበዛ አይደለምን?ለኃጢአትህም ፍጻሜ የላትም።
6 ፤ የወንድሞችህን መያዣ በከንቱ ወስደሃል፥የእርዘኞቹንም ልብስ ዘርፈሃል።
7 ፤ ለደካማ ውኃ አላጠጣህም፥ለራብተኛም እንጀራን ከልክለሃል።
8 ፤ በክንድ የበረታ ምድርን ገዛ፤ከበርቴውም ሰው ተቀመጠባት።
9 ፤ መበለቲቱን አንዳች አልባ ሰድደሃታል፤የድሀ አደጎችም ክንድ ተሰብሮአል።
10 ፤ ስለዚህ አሽክላ ከብቦሃል፥ድንገተኛ ፍርሃትም አናውጦሃል።
11 ፤ እንዳታይ ብርሃን ጨለማ ሆነችብህ፥የውኆችም ብዛት አሰጠመህ።
12 ፤ እግዚአብሔር በሰማያት ከፍ ከፍ አይልምን?ከዋክብትም እንዴት ከፍ ከፍ እንዳሉ ተመልከት።
13 ፤ አንተም። እግዚአብሔር ምን ያውቃል?በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ ሊፈርድ ይችላልን?
14 ፤ እንዳያይ የጠቈረ ደመና ጋርዶታል፤በሰማይ ክበብ ላይ ይራመዳል ብለሃል።
15 ፤ በውኑ ኃጢአተኞች ሰዎች የረገጡአትንየዱሮይቱን መንገድ ትጠብቃለህን?
16 ፤ ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፤መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ።
17 ፤ እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ፤ሁሉንም የሚችል አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል? አሉት።
18 ፤ ነገር ግን ቤታቸውን በመልካም ነገር ሞላ፤የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።
19 ፤ ጻድቃን ያዩታል፥ ደስም ይላቸዋል፤ንጹሐንም በንቀት ይስቁባቸዋል።
20 ፤ በእውነት ሀብታቸው ጠፋ፥የቀረውንም እሳት በላች።
21 ፤ አሁንም ከእርሱ ጋር ተስማማ፥ ሰላምም ይኑርህ፤በዚያም በጎነት ታገኛለህ።
22 ፤ ከአፉም ሕጉን ተቀበል፥በልብህም ቃሉን አኑር፤
23 ፤ ሁሉን ወደሚችል አምላክ ብትመለስ፥ ብትዋረድም፥ኃጢአትንም ከድንኳንህ ብታርቅ፥
24 ፤ የወርቅን ዕቃ በአፈር ውስጥ፥የኦፊርንም ወርቅ በጅረት ድንጋይ መካከል ብትጥል፥
25 ፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ወርቅና የሚብለጨለጭ ብር ይሆንልሃል።
26 ፤ የዚያን ጊዜ ሁሉን በሚችል አምላክ ደስ ይልሃል፥ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታነሣለህ።
27 ፤ ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል፤ስእለትህንም ትሰጣለህ።
28 ፤ ነገርንም ትመክራለህ፥ እርሱም ይሳካልሃል፤ብርሃንም በመንገድህ ላይ ይበራል።
29 ፤ ቢያዋርዱህ አንተ ከፍ ከፍ ትላለህ፤ትሑቱንም ሰው ያድነዋል።
30 ፤ ንጹሑን ሰው ያድነዋል፤በእጅህም ንጽሕና ትድናለህ።