መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 21

1 ፤ ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ስሙ፥ ቃሌን ስሙ፤ይህም መጽናናታችሁ ይሁን።
3 ፤ እናገር ዘንድ ተዉኝ፤ከተናገርሁም በኋላ ተሳለቁ።
4 ፤ በውኑ የኀዘን እንጉርጕሮዬ ለሰው እናገራለሁን?አለመታገሥ ስለ ምን አይገባኝም?
5 ፤ ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ተደነቁም፤እጃችሁንም በአፋችሁ ላይ አኑሩ።
6 ፤ እኔ ባሰብሁ ቍጥር እጨነቃለሁ፥ፃዕርም ሥጋዬን ይይዛል።
7 ፤ ስለ ምን ኃጢአተኞች በሕይወት ይኖራሉ?ስለ ምንስ ያረጃሉ? በባለጠግነትስ ስለ ምን ይበረታሉ?
8 ፤ ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፥ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው።
9 ፤ ቤታቸው ከፍርሃት ወጥቶ የታመነ ነው፥የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።
10 ፤ ኮርማቸው ይወልዳል፥ ዘሩንም አይጥለውም፤ላማቸውም ትወልዳለች፥ አትጨነግፍም።
11 ፤ ሕፃናቶቻቸውን እንደ መንጋ ያወጣሉ፥ልጆቻቸውም ይዘፍናሉ።
12 ፤ ከበሮና መሰንቆ ወስደው ይዘምራሉ፥በእምቢልታ ድምፅ ደስ ይላቸዋል።
13 ፤ ዕድሜያቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ፤ድንገትም ወደ ሲኦል ይወርዳሉ።
14 ፤ እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ፤መንገድህን እናውቅ ዘንድ አንወድድም።
15 ፤ እናመልከውስ ዘንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ማን ነው?ወይስ ወደ እርሱ ብንጸልይ ምን ይጠቅመናል? ይላሉ።
16 ፤ እነሆ፥ ሀብታቸው በእጃቸው ውስጥ አይደለምን?የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።
17 ፤ የኃጥአን መብራት የጠፋው፥መቅሠፍትም የመጣባቸው፥እግዚአብሔርም በቍጣው መከራ የከፈላቸው፥
18 ፤ በነፋስ ፊት እንደ ገለባ፥ዐውሎ ነፋስም እንደሚወስደው ትቢያ የሆኑ ስንት ጊዜ ነው?
19 ፤ እናንተ። እግዚአብሔር በደላቸውን ለልጆቻቸው ይጠብቃል ብላችኋል።እነርሱ ያውቁ ዘንድ ፍዳን ለራሳቸው ይክፈል።
20 ፤ ዓይኖቻቸው ጥፋታቸውን ይዩ፥ሁሉን ከሚችል አምላክ ቍጣ ይጠጡ።
21 ፤ የወራታቸውስ ቍጥር ቢቈረጥ፥ከእነርሱ በኋላ የቤታቸው ደስታ ምን ይሆናቸዋል?
22 ፤ ከፍ ከፍ ባሉትስ ላይ ለሚፈርድ ለእግዚአብሔርበውኑ ሰው እውቀትን ያስተምራልን?
23 ፤ አንድ ሰው በሰላም ተዘልሎ ሲቀመጥበሙሉ ኃይሉ ሳለ ይሞታል።
24 ፤ በአንጀቱ ውስጥ ስብ ሞልቶአል፥የአጥንቶቹም ቅልጥም ረጥቦአል።
25 ፤ ሌላውም ሰው መልካምን ነገር ከቶ ሳይቀምስበተመረረች ነፍስ ይሞታል።
26 ፤ በአፈር ውስጥ በአንድ ላይ ይተኛሉ፥ትልም ይከድናቸዋል።
27 ፤ እነሆ፥ አሳባችሁን፥የመከራችሁብኝንም ክፉ ምክር አውቄዋለሁ።
28 ፤ እናንተ። የከበርቴው ቤት የት ነው?ኃጢአተኛውም ያደረበት ድንኳን የት ነው? ብላችኋል።
29 ፤ መንገድ አላፊዎችን አልጠየቃችሁምን?ምልክታቸውን አታውቁምን?
30 ፤ ኃጢአተኛው በመቅሠፍት ቀን እንደ ተጠበቀ፥በቍጣው ቀን እንደሚድን።
31 ፤ መንገዱን በፊቱ የሚናገር ማን ነው?የሠራውንስ የሚመልስበት ማን ነው?
32 ፤ እርሱን ግን ወደ መቃብር ይሸከሙታል፥ሰዎቹም በመቃብሩ ላይ ይጠብቃሉ።
33 ፤ የሸለቆው ጓል ይጣፍጥለታል፤በኋላውም ሰው ሁሉ ይሳባል፥በፊቱም ቍጥር የሌለው ጉባኤ አለ።
34 ፤ የምትመልሱልኝ ውስልትና ነውናበከንቱ እንዴት ታጽናኑኛላችሁ?