መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 29
1 ፤ ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ።
2 ፤ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ፥እንደ ፊተኛው ወራት ምነው በሆንሁ!
3 ፤ በራሴ ላይ መብራቱ በበራ ጊዜ፥እኔም ጨለማውን አልፌ በብርሃኑ በሄድሁ ጊዜ፥
4 ፤ በሙሉ ሰውነቴ እንደ ነበርሁ ጊዜ፥እግዚአብሔር ድንኳኔን በጋረደ ጊዜ፥
5 ፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ከእኔ ጋር ገና ሳለ፥ልጆቼም በዙሪያዬ ሳሉ፥
6 ፤ መንገዴ በቅቤ ይታጠብ በነበረ ጊዜ፥ድንጋዩ የዘይት ፈሳሽ ያፈስስልኝ በነበረ ጊዜ።
7 ፤ ወደ ከተማይቱ በር በወጣሁ ጊዜ፥በአደባባዩም ወንበሬን ባኖርሁ ጊዜ፥
8 ፤ ጐበዛዝት እኔን አይተው ተሸሸጉ፥ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ።
9 ፤ አለቆቹ ከመናገር ዝም አሉ፥እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ጫኑ።
10 ፤ የታላላቆቹም ድምፅ አረመመ፤ምላሳቸውም በትናጋቸው ተጣጋ።
11 ፤ የሰማችኝ ጆሮ አሞገሰችኝ፥ያየችኝም ዓይን መሰከረችልኝ፤
12 ፤ የሚጮኸውን ችግረኛ፥ድሀ አደጉንና ረጂ የሌለውን አድኜ ነበርሁና።
13 ፤ ለጥፋት የቀረበው በረከት በላዬ መጣ፤የባልቴቲቱንም ልብ እልል አሰኘሁ።
14 ፤ ጽድቅን ለበስሁ እርስዋም ለበሰችኝ፤ፍርዴም እንደ መጐናጸፊያና እንደ ኵፋር ነበረ።
15 ፤ ለዕውር ዓይን፥ለአንካሳ እግር ነበርሁ።
16 ፤ ለድሀው አባት ነበርሁ፤የማላውቀውንም ሰው ሙግት መረመርሁ።
17 ፤ የኃጢአተኛውን መንጋጋ ሰበርሁ፥የነጠቀውንም ከጥርሱ ውስጥ አስጣልሁ።
18 ፤ እኔም አልሁ። በልጆቼ መካከል እሞታለሁ፥ዕድሜዬንም እንደ አሸዋ አበዛለሁ፤
19 ፤ ሥሬ በውኃ ላይ ተዘርግቶአል፥ጠልም በቅርንጫፌ ላይ ያድራል፤
20 ፤ ክብሬ በእኔ ዘንድ ታድሶአል፥ቀስቴም በእጄ ውስጥ ለምልሞአል።
21 ፤ ሰዎች እኔን ሰምተው በትዕግሥት ተጠባበቁ፥ምክሬንም ለማዳመጥ ዝም አሉ።
22 ፤ ከቃሌ በኋላ አንዳች አልመለሱም፤ንግግሬም በእርሱ ላይ ተንጠባጠበ።
23 ፤ ዝናብን እንደሚጠብቁ በትዕግሥት ጠበቁኝ፤የጥቢን ዝናብ እንደሚሹ አፋቸውን ከፈቱ።
24 ፤ እነርሱ ባልታመኑ ጊዜ ሳቅሁላቸው፤የፊቴንም ብርሃን አላወረዱም።
25 ፤ መንገዳቸውን መረጥሁ፤እንደ አለቃ ሆኜ ተቀመጥሁ፤ንጉሥ በሠራዊቱ መካከል እንደሚኖር፥ኅዘነተኞችን እንደሚያጽናና ኖርሁ።