መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 24

1 ፤ ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ ዘመናት አልተሰወረምናእርሱን የሚያውቁ ለምን ወራቱን አያዩም?
2 ፤ የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፤መንጋዎቹን በዝብዘው ያሰማራሉ።
3 ፤ የድሀ አድጎቹን አህያ ይነዳሉ፤የመበለቲቱን በሬ ስለ መያዣ ይወስዳሉ።
4 ፤ ድሆቹን ከመንገዱ ያወጣሉ፤የምድርም ችግረኞች ሁሉ ይሸሸጋሉ።
5 ፤ እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች፥መብልን ፈልገው ወደ ሥራቸው ይወጣሉ፤ምድረ በዳውም ለልጆቻቸው መብልን ይሰጣቸዋል።
6 ፤ እነዚያ በእርሻ ውስጥ እህላቸውን ያጭዳሉ፤የበደለኛውንም ወይን ይቃርማሉ።
7 ፤ ራቁታቸውን ያለ ልብስ ያድራሉ፥በብርድ ጊዜ መጐናጸፊያ የላቸውም።
8 ፤ ከተራሮች በሚወርድ ዝናብ ይረጥባሉ፤መጠጊያም አጥተው ቋጥኙን ያቅፋሉ።
9 ፤ ድሀ አደጉን ልጅ ከጡቱ የሚነጥሉ አሉከችግረኛውም መያዣ ይወስዳሉ።
10 ፤ ያለ ልብስ ራቁታቸውን ይሄዳሉ፤ተርበውም ነዶዎችን ይሸከማሉ፤
11 ፤ በእነዚህ ሰዎች አጥር ውስጥ ዘይት ያደርጋሉ፤ወይንም ይጠምቃሉ፥ ነገር ግን ይጠማሉ።
12 ፤ ከከተማውና ከገዛ ቤቶቻቸው ይባረራሉ፤የልጆችም ነፍስ ለእርዳታ ትጮኻለች፤እግዚአብሔር ግን ስንፍናቸውን አይመለከትም።
13 ፤ እነዚህ በብርሃን ላይ የሚያምፁ ናቸው፤መንገዱን አያውቁም፥ በጎዳናውም አይጸኑም።
14 ፤ ነፍሰ ገዳዩም ሳይነጋ ማልዶ ይነሣል፤ችግረኞችንና ድሆችን ይገድላል፤በሌሊትም እንደ ሌባ ነው።
15 ፤ የአመንዝራም ዓይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል።የማንም ዓይን አያየኝም ይላል፥ፊቱንም ይሸፍናል።
16 ፤ ቤቶቹን በጨለማ ይነድላሉ፤በቀን ይሸሸጋሉ፤ብርሃንም አያውቁም።
17 ፤ የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፤የሞትን ጥላ ድንጋጤ ያውቃሉና።
18 ፤ እነርሱ በውኃ ፊት ላይ በርረው ያልፋሉ፤እድል ፈንታቸውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፤ወደ ወይኑ ቦታ መንገድ አይዞሩም።
19 ፤ ድርቅና ሙቀት የአመዳዩን ውኃ ያጠፋሉ፤እንዲሁ ሲኦል በደለኞችን ታጠፋለች።
20 ፤ ማኅፀን ትረሳዋለች፤ትልም በደስታ ይጠባዋል፤ዳግመኛም አይታሰብም፤ክፋትም እንደ ዛፍ ይሰበራል።
21 ፤ የማትወልደውን መካኒቱን ይበድላታል፤ለመበለቲቱም በጎነት አያደርግም።
22 ፤ ነገር ግን በኃይሉ ኃያላንን ይስባል፤እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም።
23 ፤ እግዚአብሔር በደኅና አኑሮአቸዋል፥በዚያም ይታመናሉ፤ዓይኖቹ ግን በመንገዳቸው ላይ ናቸው።
24 ፤ ጥቂት ጊዜ ከፍ ከፍ ይላሉ፤ይሄዳሉ፥ ይጠወልጋሉም፤እንደ ሌሎች ሁሉ ይከማቻሉ፤እንደ እሸትም ራስ ይቈረጣሉ።
25 ፤ እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ የሚያደርገኝ፥ነገሬንስ እንደ ምናምን የሚያደርገው ማን ነው?