መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 28
1 ፤ በእውነት ብር የሚወጣበት፥ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ።
2 ፤ ብረት ከመሬት ውስጥ ይወሰዳል፤መዳብም ከድንጋይ ይቀለጣል።
3 ፤ ሰው ለጨለማ ፍጻሜን ያደርጋል፤የጨለማውንና የሞት ጥላን ድንጋይ እስከ ወሰኑ ድረስ ይፈላልጋል።
4 ፤ ሰው ከሚኖርበት ርቀው መውረጃ ይቈፍራሉ፤ከሰውም እግር ተረሱ፥ከሰዎችም ርቀው እየተንጠለጠሉ ይወዛወዛሉ።
5 ፤ እንጀራ ከምድር ውስጥ ይወጣል፤በእሳትም እንደሚሆን ታችኛው ይገለበጣል።
6 ፤ ድንጋይዋ የሰንፔር ስፍራ ነው፥የወርቅም ድቃቂ አለው።
7 ፤ መንገድዋን ጭልፊት አያውቀውም፥የአሞራም ዓይን አላየውም።
8 ፤ የትዕቢት ልጆች አልረገጡአትም፥ደቦል አንበሳ አላለፈባትም።
9 ፤ ሰው ወደ ቡላድ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፥ተራራውንም ከመሠረቱ ይገለብጣል።
10 ፤ ከድንጋይ ውስጥ መንዶልዶያ ይወቅራል፤ዓይኑም ዕንቍን ሁሉ ታያለች።
11 ፤ ፈሳሹም እንዳይንጠባጠብ ይገድባል፤የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።
12 ፤ ነገር ግን ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው?የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?
13 ፤ ሰው መንገድዋን አያውቅም፤በሕያዋን ምድር አትገኝም።
14 ፤ ቀላይ። በእኔ ውስጥ የለችም ይላል፤ባሕርም። በእኔ ዘንድ የለችም ይላል።
15 ፤ በምዝምዝ ወርቅ አትገኝም፥ብርም ስለ ዋጋዋ አይመዘንም።
16 ፤ በኦፊር ወርቅ፥በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም።
17 ፤ ወርቅና ብርጭቆ አይወዳደሩአትም፥በጥሩ ወርቅም ዕቃ አትለወጥም።
18 ፤ ስለ ዛጐልና ስለ አልማዝ አይነገርም።የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቍ ይልቅ ይበልጣል።
19 ፤ የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን አይተካከላትም፥በጥሩም ወርቅ አትገመትም።
20 ፤ እንግዲያሳ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች?የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?
21 ፤ ከሕያዋን ሁሉ ዓይን ተሰውራለች፥ከሰማይ ወፎች ተሸሽጋለች።
22 ፤ ጥፋትና ሞት። ወሬዋን በጆሮቻችን ሰማን ብለዋል።
23 ፤ እግዚአብሔር መንገድዋን ያስተውላል፥እርሱም ስፍራዋን ያውቃል።
24 ፤ እርሱም የምድርን ዳርቻ ይመለከታል፥ከሰማይም በታች ያለውን ሁሉ ያያል።
25 ፤ ለነፋስ ሚዛንን ባደረገለት ጊዜ፥ውኆችንም በስፍር በሰፈረ ጊዜ፥
26 ፤ ለዝናብም ሥርዓትን፥ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን ባደረገ ጊዜ፥
27 ፤ በዚያን ጊዜ አያት፥ ገለጣትም፤አዘጋጃትም፥ ደግሞም መረመራት።
28 ፤ ሰውንም። እነሆ፥ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ከኃጢአትም መራቅ ማስተዋል ነው አለው።