መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 31

1 ፤ ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁ፤እንግዲህስ ቈንጆይቱን እንዴት እመለከታለሁ?
2 ፤ የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ከላይ፥ሁሉንም የሚችል አምላክ ርስት ከአርያም ምንድር ነው?
3 ፤ መዓትስ ለኃጢአተኛ፥መለየትስ ለሚበድሉ አይደለምችን?
4 ፤ መንገዴን አያይምን?እርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን?
5 ፤6፤ በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥እግዚአብሔርም ቅንነቴን ይወቅ።በሐሰት ሄጄ እንደ ሆነእግሬም ለሽንገላ ቸኵላ እንደ ሆነ፥
7 ፤ እርምጃዬ ከመንገድ ፈቀቅ ብሎ፥ልቤም ዓይኔን ተከትሎ፥ነውርም ከእጄ ጋር ተጣብቆ እንደ ሆነ፥
8 ፤ እኔ ልዝራ፥ ሌላ ሰውም ይብላው፤የሚበቅለውም ሁሉ ይነቀል።
9 ፤ ልቤ ወደ ሌላይቱ ሴት ጐምጅቶ እንደ ሆነ፥በባልንጀራዬም ደጅ አድብቼ እንደ ሆነ፥
10 ፤ ሚስቴ ለሌላ ሰው ትፍጭ፥ሌሎችም በእርስዋ ላይ ይጐንበሱ።
11 ፤ ይህ ክፉ አበሳ፥ፈራጆችም የሚቀጡበት በደል ነውና፤
12 ፤ ይህ እስከ ጥፋት ድረስ የሚበላ እሳት፥ቡቃያዬንም ሁሉ የሚነቅል ነውና።
13 ፤ ወንድ ባሪያዬ ወይም ሴት ባሪያዬ ከእኔ ጋር በተምዋገቱ ጊዜ፥ሙግታቸውን ንቄ እንደ ሆነ፥
14 ፤ እግዚአብሔር በተነሣ ጊዜ ምን አደርጋለሁ?በጐበኘኝ ጊዜ ምን እመልስለታለሁ?
15 ፤ እኔን በማኅፀን የፈጠረ እርሱንስ የፈጠረው አይደለምን?በማኅፀንስ ውስጥ የሠራን አንድ አይደለንምን?
16 ፤ ድሀውን ከልመናው ከልክዬ፥የመበለቲቱን ዓይን አጨልሜ እንደ ሆነ፥
17 ፤ እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፥ድሀ አደጉም ደግሞ ከእርሱ ሳይበላ ቀርቶ እንደ ሆነ፤
18 ፤ እርሱን ግን ከታናሽነቴ ጀምሬ እንደ አባቱ ከእኔ ጋር አሳድጌው ነበር፥እርስዋንም ከእናቴ ማኅፀን ጀምሬ መራኋት፤
19 ፤ ራቁቱን የሆነው ሰው ሲጠፋ፥ወይም ድሀ ያለ ልብስ ሲሆን አይቼ እንደ ሆነ፥
20 ፤ ጐንና ጐኑ ያልባረከችኝ፥በበጎቼም ጠጕር ያልሞቀ እንደ ሆነ፤
21 ፤ በበሩ ረዳት ስላየሁ፥በድሀ አደጉ ላይ እጄን አንሥቼ እንደ ሆነ፥
22 ፤ ትከሻዬ ከመሠረትዋ ትውደቅ፥ክንዴም ከመገናኛዋ ትሰበር።
23 ፤ የእግዚአብሔር መዓት አስደንግጦኛልና፤በክብሩም ፊት ምንም ለማድረግ አልቻልሁም።
24 ፤ ወርቅን ተስፋ አድርጌ፥ጥሩውንም ወርቅ። በአንተ እታመናለሁ ብዬ እንደ ሆነ፤
25 ፤ ሀብቴ ስለ በዛ፥እጄም ብዙ ስላገኘች ደስ ብሎኝ እንደ ሆነ፤
26 ፤ ፀሐይ ሲበራጨረቃ በክብር ስትሄድ አይቼ፥
27 ፤ ልቤ በስውር ተታልሎ፥አፌም እጄን ስሞ እንደ ሆነ፤
28 ፤ ልዑል እግዚአብሔርን በካድሁ ነበርናይህ ደግሞ ፈራጆች የሚቀጡበት በደል በሆነ ነበር።
29 ፤ በሚጠላኝ መጥፋት ደስ ብሎኝክፉ ነገርም ባገኘው ጊዜ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ፤
30 ፤ ነገር ግን በመርገም ነፍሱን በመሻትአንደበቴን ኃጢአት ይሠራ ዘንድ አልሰጠሁም፤
31 ፤ በድንኳኔ የሚኖሩ ሰዎች።በከብቱ ሥጋ ያልጠገበ ማን ይገኛል? ብለው እንደ ሆነ፤
32 ፤ መጻተኛው ግን በሜዳ አያድርም ነበር፥ደጄንም ለመንገደኛ እከፍት ነበር፤
33 ፤ በደሌንም በብብቴ በመሸሸግኃጢአቴን እንደ ሰው ሰውሬ እንደ ሆነ፤
34 ፤ ከሕዝብ ብዛት ፈርቼ፥የዘመዶቼም ንቀት አስደንግጦኝ፥ዝም ብዬ ከደጅ ያልወጣሁ እንደ ሆነ፤
35 ፤ የሚያዳምጠኝ ምነው በኖረልኝ!እነሆ የእጄ ምልክትሁሉን የሚችል አምላክ ይመልስልኝ፤ከባላጋራዬ የተጻፈው የክስ ጽሑፍ ምነው በተገኘልኝ!
36 ፤ በትከሻዬ ላይ እሸከመው፥አክሊልም አድርጌ በራሴ አስረው ነበር፤
37 ፤ የእርምጃዬን ቍጥር አስታውቀው፥እንደ አለቃም ሆኜ አቀርብለት ነበር።
38 ፤ እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ እንደ ሆነ፥ትልሞችዋም በአንድ ላይ አልቅሰው እንደ ሆነ፤
39 ፤ ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፥የባለቤቶችንም ነፍስ አሳዝኜ እንደ ሆነ፥
40 ፤ በስንዴ ፋንታ አሜከላ፥በገብስም ፋንታ ኵርንችት ይውጣብኝ። የኢዮብ ቃል ተፈጸመ።