መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 13

1 ፤ እነሆ፥ ይህን ሁሉ ዓይኔ አየች፤ጆሮዬም ሰምታ አስተዋለችው።
2 ፤ እናንተ የምታውቁትን እኔ ደግሞ አውቃለሁ፤ከእናንተ የማንስ አይደለሁም።
3 ፤ ነገር ግን ሁሉን ለሚችል አምላክ መናገር እፈልጋለሁ፥ከእግዚአብሔርም ጋር ለመዋቀስ እሻለሁ።
4 ፤ እናንተ ግን በሐሰት ለባጮች ናችሁ፤ሁላችሁ የማትጠቅሙ ባለ መድኃኒቶች ናችሁ።
5 ፤ ምነው ዝም ብላችሁ ብትኖሩ!ይህ ጥበብ በሆነላችሁ ነበር።
6 ፤ አሁንም ክርክሬን ስሙ፥የከንፈሬንም ሙግት አድምጡ።
7 ፤ በውኑ ስለ እግዚአብሔር ሐሰትን ትናገራላችሁን?ስለ እርሱም ሽንገላን ታወራላችሁን?
8 ፤ ለፊቱስ ታደላላችሁን?ስለ እግዚአብሔርስ ትከራከራላችሁን?
9 ፤ ቢመረምራችሁስ መልካም ይሆንልችኋልን?ወይስ በሰው እንደምትሳለቁ ትሳለቁበታላችሁን?
10 ፤ በስውር ለሰው ፊት ብታደሉዘለፋ ይዘልፋችኋል።
11 ፤ ክብሩስ አያስፈራችሁምን?ግርማውስ አይወድቅባችሁምን?
12 ፤ ምስሌዎቻችሁ የአመድ ምሳሌዎች ናቸው፤ምሽጎቻችሁ የጭቃ ምሽጎች ናቸው።
13 ፤ ዝም በሉ፥ እናገርም ዘንድ ተዉኝ፤የሆነው ነገር ይምጣብኝ።
14 ፤ ሥጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ፥ሕይወቴንም በእጄ አኖራለሁ።
15 ፤ እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፤ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ።
16 ፤ ዝንጉ ሰው በፊቱ አይገባምናእርሱ መድኃኒት ይሆንልኛል።
17 ፤ ነገሬን ተግታችሁ ስሙ፥ምስክርነቴንም በጆሮአችሁ አድምጡ።
18 ፤ እነሆ፥ ሙግቴን አዘጋጅቻለሁ።እንደምጸድቅም አውቃለሁ።
19 ፤ ከእኔስ ጋር የሚፋረድ ማን ነው?አሁን እኔ ዝም ብል እሞታለሁ።
20 ፤ ነገር ግን ሁለት ነገር አታድርግብኝ፤የዚያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፤
21 ፤ እጅህን ከእኔ አርቅ፤ግርማህም አታስደንግጠኝ።
22 ፤ ከዚያም በኋላ ጥራኝ፥ እኔም እመልስልሃለሁ።ወይም እኔ ልናገር፥ አንተም መልስልኝ።
23 ፤ ያለብኝስ በደልና ኃጢአት ምን ያህል ነው?መተላለፌንና ኃጢአቴን አስታውቀኝ።
24 ፤ ፊትህን ከእኔ የሰወርህ፥እንደ ጠላትህም የቈጠርኸኝ ስለ ምን ነው?
25 ፤ የረገፈውን ቅጠል ታስጨንቃለህን?ወይስ የደረቀውን ዕብቅ ታሳድዳለህን?
26 ፤ የመረረ ነገር ጽፈህብኛልና፤የሕፃንነቴንም ኃጢአት ታወርሰኛለህ።
27 ፤ እግሬንም በእግር ግንድ አግብተሃል፥መንገዴንም ሁሉ መርምረሃል፤የእግሬን ፍለጋ ወስነሃል።
28 ፤ እኔ እንደሚጠፋ በስባሳ ነገር፥ብልም እንደሚበላው ልብስ ነኝ።