መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 10

1 ፤ ነፍሴ ሕይወቴን ሰለቸቻት፤የኀዘን እንጕርጕሮዬን እለቀዋለሁ፤በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ።
2 ፤ እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ።አትፍረድብኝ፤ የምትከራከረኝ ለምን እንደ ሆነ ንገረኝ።
3 ፤ ልታስጨንቅና የእጅህን ሥራ ልትንቅየኃጥአንንስ ምክር ልታበራበአንተ ዘንድ መልካም ነውን?
4 ፤ በውኑ የሥጋ ዓይን አለህን?ወይስ ሰው እንደሚያይ ታያለህን?
5 ፤6፤ ወይስ ክፋቴን ትፈላለግ ዘንድ፥ኃጢአቴንም ትመረምር ዘንድ፥ዘመንህ እንደ ሰው ዘመን ነውን?ወይስ ዓመታትህ እንደ ሰው ዓመታት ናቸውን?
7 ፤ ከዚህም በላይ በደለኛ እንዳልሆንሁ፥ከእጅህም የሚያድን እንደሌለ አንተ ታውቃለህ።
8 ፤ እጅህ ለወሰችኝ ሠራችኝም፤ከዚያም በኋላ ዞረህ ታጠፋኝ ዘንድ ፈለግህ።
9 ፤ እንደ ጭቃ አድርገህ እንደ ለወስኸኝ አስብ፤ወደ ትቢያም ትመልሰኛለህን?
10 ፤ በውኑ እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን?እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን?
11 ፤ ቁርበትና ሥጋ አለበስኸኝ፥በአጥንትና በጅማትም አጠንከርኸኝ።
12 ፤ ሕይወትና ቸርነት አደረግህልኝ፤መጐብኘትህም መንፈሴን ጠበቀች።
13 ፤ እነዚህንም ነገሮች በልብህ ውስጥ ሰወርህ።ይህ ሁሉ በአሳብህ እንዳለ አውቃለሁ።
14 ፤ ኃጢአት ብሠራ አንተ ትመለከተኛለህ፤ከኃጢአቴም ንጹሕ አታደርገኝም።
15 ፤ በደለኛ ብሆን ወዮልኝ፤ጻድቅም ብሆን ራሴን አላነሣም፤ጕስቍልናን ተሞልቻለሁ፥መከራዬንም ተመልክቻለሁ።
16 ፤ ራሴም ከፍ ከፍ ቢል እንደ አንበሳ ታድነኛለህ፤ተመልሰህም ድንቅ ነገር ታድርግብኛለህ
17 ፤ ምስክሮችህን ታድስብኛለህ፤ቍጣህንም ታበዛብኛለህ፤ጭፍራ በጭፍራ ላይ ትጨምርብኛለህ።
18 ፤ ስለ ምን ከማኅፀን አወጣኸኝ?ዓይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ።
19 ፤ እንዳልነበረ በሆንሁ፤ከማኅፀንም ወደ መቃብር በወሰዱኝ።
20 ፤ የሕይወቴ ዘመን ጥቂት አይደለምን?
21 ፤ ወደማልመለስበት ስፍራ፥ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ ምድር፥
22 ፤ እንደ ጨለማም ወደ ጨለመች፥ሥርዓትም ወደሌለባት ወደ ሞት ጥላ፥ብርሃንዋም እንደ ጨለማ ወደ ሆነ ምድር ሳልሄድ፥ጥቂት እጽናና ዘንድ ተወኝ፥ ልቀቀኝም።