መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 16
1 ፤ ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ እንደዚህ ያለ ዓይነት ነገር እጅግ ሰማሁ፤እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ።
3 ፤ በውኑ ከንቱ ቃል ይፈጸማልን?ወይስ ትመልስ ዘንድ ያነሣሣህ ምንድር ነው?
4 ፤ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ እናገር ዘንድ ይቻለኝ ነበር፤ነፍሳችሁ በነፍሴ ፋንታ ቢሆን ኖሮ፥እኔ በእናንተ ላይ ቃል ማሳካት፥ራሴንም በእናንተ ላይ መነቅነቅ በተቻለኝ ነበር።
5 ፤ በአፌም ነገር ባበረታኋችሁ ነበር፤የከንፈሬን ማጽናናት ባልከለከልሁም ነበር።
6 ፤ እኔ ብናገር ሕማሜ አይቀነስም፤ዝምም ብል ከእኔ አይወገድም።
7 ፤ አሁን ግን አድክሞኛል፤ወገኔንም ሁሉ አፍርሰሃል።
8 ፤ መጨማተሬ ይመሰክርብኛል፤ክሳቴም ተነሥቶብኛል፤በፊቴም ይመሰክርብኛል።
9 ፤ በቍጣው ቀደደኝ፥ እርሱም ጠላኝ፤ጥርሶቹንም አፋጨብኝ፤ጠላቴ ዓይኑን አፈጠጠብኝ፤
10 ፤ እነርሱም አፋቸውን ከፈቱብኝ፤እያላገጡ ጕንጬን ጠፈጠፉኝ፤በአንድነትም ተሰበሰቡብኝ።
11 ፤ እግዚአብሔር ለጠማማ ሰው አሳልፎ ሰጠኝ፥በክፉዎችም እጅ ጣለኝ።
12 ፤ ተዘልዬ ተቀምጬ ነበር፥ እርሱም ሰበረኝ፤አንገቴንም ይዞ ቀጠቀጠኝ፤እንደ ዓላማ አድርጎ አቆመኝ።
13 ፤ ቀስተኞቹ ከበቡኝ፤ኵላሊቴንም ቈራረጠ፥ እርሱም አልራራም፤ሐሞቴን በምድር ላይ አፈሰሰ።
14 ፤ በቍስል ላይ ቍስል ጨመረብኝ፤እንደ ኃያል እየሠገገ ይሮጥብኛል።
15 ፤ በቁርበቴ ላይ ማቅ ሰፋሁ፥ቀንዴንም በመሬት ላይ አኖርሁ።
16 ፤ ፊቴ ከልቅሶ የተነሣ ቀላ፤የሞት ጥላ በዓይኖቼ ቆብ ላይ አለ፤
17 ፤ ነገር ግን በእጄ ዓመፅ የለም፤ጸሎቴም ንጹሕ ነው።
18 ፤ ምድር ሆይ፥ ደሜን አትክደኚ፥ለጩኸቴም ማረፊያ አይሁን።
19 ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ምስክሬ በሰማይ አለ፥የሚመሰክርልኝም በአርያም ነው።
20 ፤ ጸሎቴ ወደ እግዚአብሔር ይድረስ፥ዓይኔም በፊቱ እንባ ታፍስስ።
21 ፤ የሰው ልጅ ከባልንጀራው ጋር እንደሚምዋገት፥ሰው በእግዚአብሔር ፊት ለመምዋገት ምነው በቻለ!
22 ፤ ጥቂቶች ዓመታት ካለፉ በኋላእኔ ወደማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ።