መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 6
1 ፤ ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ ትካዜዬ ምነው በተመዘነ ኖሮ!መከራዬም ሁሉ ምነው በሚዛን ላይ በተደረገ ኖሮ!
3 ፤ ከባሕር አሸዋ ይልቅ ይከብድ ነበርና፤ስለዚህ ቃሌ ደፋር ሆኖአል።
4 ፤ ሁሉን የሚችል የአምላክ ፍላጻ በሥጋዬ ውስጥ ነው፥መርዙንም ነፍሴ ትጠጣለች፤የእግዚአብሔር ድንጋጤ በላዬ ተሰልፎአል።
5 ፤ በውኑ የሜዳ አህያ ሣር ሳለው ይጮኻልን?ወይስ በሬ ገለባ ሳለው ይጮኻልን?
6 ፤ የማይጣፍጥስ ነገር ያለ ጨው ይበላልን?ወይስ የእንቁላል ውኃ ይጥማልን?
7 ፤ ሰውነቴ ትነካው ዘንድ እንቢ አለችው፤እንደሚያስጸይፍ መብል ሆነብኝ።
8 ፤ ልመናዬ ምነው በደረሰልኝ!እግዚአብሔርም ምኞቴን ምነው በሰጠኝ!
9 ፤ እግዚአብሔርም ያደቀኝ ዘንድእጁንም ለቅቆ ያጠፋኝ ዘንድ ወድዶ ቢሆን ኖሮ!
10 ፤ መጽናናት በሆነልኝ ነበር፤በማይራራ ሕመም ሐሤት ባደረግሁ ነበር፥የቅዱሱን ቃል አልካድሁምና።
11 ፤ እጠብቅ ዘንድ ጕልበቴ ምንድር ነው?እታገሥም ዘንድ ፍጻሜዬ ምንድር ነው?
12 ፤ ጕልበቴ የድንጋይ ጕልበት ነውን?ሥጋዬስ እንደ ናስ ነውን?
13 ፤ በውኑ ረድኤት በእኔ እንደሌለጥበብም ሁሉ ከእኔ ዘንድ እንደ ተባረረ አይደለምን?
14 ፤ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን መፍራትለሚተው፥ ለመዛል ለቀረበው ስንኳወዳጁ ቸርነትን ሊያሳይ ይገባል።
15 ፤ ወንድሞቼ እንደ ፈፋ፥እንደሚያልፍ ፈፋ ሐሰተኞች ሆኑብኝ።
16 ፤ ከበረዶ የተነሣ ደፈረሱ፥አመዳይም ተሰወረባቸው፤
17 ፤ ፀሐይ በተኰሰች ጊዜ ይደርቃሉ፤በሙቀትም ጊዜ ከስፍራቸው ይጠፋሉ።
18 ፤ በየዳርቻቸውም የሚሄዱ ነጋዴዎች ፈቀቅ ይላሉ፤ወደ በረሃ ወጥተው ይጠፋሉ።
19 ፤ የቴማን ነጋዴዎች ተመለከቱ፥የሳባ መንገደኞችም ተጠባበቁአቸው።
20 ፤ ተስፋ አድርገዋቸው ነበርና አፈሩ፤ወደዚያ ደረሱ፥ እፍረትም ያዛቸው።
21 ፤ አሁንም እናንተ እንደዚሁ ሆናችኋል፤መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ።
22 ፤ በውኑ። አንዳች ነገር አምጡልኝ፤ወይስ። ከብልጥግናችሁ ስጦታ አቅርቡልኝ፤
23 ፤ ወይስ። ከጠላቴ እጅ አስጥሉኝ፤ወይስ። ከአስጨናቂው እጅ አድኑኝ አልኋችሁን?
24 ፤ አስተምሩኝ፥ እኔም ዝም እላለሁ፤የተሳሳትሁትንም ንገሩኝ።
25 ፤ የቅንነት ቃል እንዴት ኃይለኛ ነው!የእናንተ ሙግት ግን ምን ይገሥጻል?
26 ፤ ተስፋ የሌለው ሰው ንግግር እንደ ነፋስ ነውናቃሌን ትገሥጹ ዘንድ ታስባላችሁን?
27 ፤ በድሀ አደጉ ላይ ዕጣ ትጣጣላላችሁ፤ለወዳጆቻችሁም ጕድጓድ ትቈፍራላችሁ።
28 ፤ አሁንም፥ እባካችሁ፥ ወደ እኔ ተመልከቱ፤በፊታችሁም ሐሰት አልናገርም።
29 ፤ እባካችሁ፥ ተመለሱ፤ በደል አይሁን፤ጽድቄ በዚህ ነገር ነውና አንድ ጊዜ ተመለሱ።
30 ፤ በውኑ በአንደበቴ በደል ይገኛልን?አፌስ ተንኰልን ይለይ ዘንድ አይችልምን?