መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 7

1 ፤ በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን?ወራቱም እንደ ምንደኛ ወራት አይደለምን?
2 ፤ አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥
3 ፤ እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ።
4 ፤ በተኛሁ ጊዜ። መቼ እነሣለሁ? እላለሁ።ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥እስኪነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ።
5 ፤ ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፤ቁርበቴ ያፈከፍካል እንደ ገናም ይመግላል።
6 ፤ ዘመኔ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ይቸኵላል፥ያለ ተስፋም ያልቃል።
7 ፤ ሕይወቴ እስትንፋስ እንደ ሆነ አስብ፤ዓይኔ መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ አያይም።
8 ፤ የሚያየኝ ሰው ዓይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፤ዓይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፥ እኔም አልገኝም።
9 ፤ ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ፥እንዲሁ ወደ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም።
10 ፤ ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፥ስፍራውም ዳግመኛ አያውቀውም።
11 ፤ ስለዚህም አፌን አልከለክልም፤በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፤በነፍሴ ምሬት በኀዘን አንጐራጕራለሁ።
12 ፤ ጠባቂ ታስነሣብኝ ዘንድ፥እኔ ባሕር ወይስ አንበሪ ነኝን?
13 ፤ እኔም። አልጋዬ ያጽናናኛል፥መኝታዬም የኀዘን እንጕርጕሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥
14 ፤ አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥በራእይም ታስደነግጠኛለህ፤
15 ፤ ነፍሴም ከአጥንቴ ይልቅመታነቅንና ሞትን መረጠች።
16 ፤ ሕይወቴን ናቅኋት፤ ለዘላለም ልኖር አልወድድም።የሕይወቴ ዘመን እስትንፋስ ነውና ተወኝ።
17 ፤ ሰው ምንድር ነው ታከብረው ዘንድ፥ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥
18 ፤ ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ?
19 ፤ የማትተወኝ እስከ መቼ ነው?ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው?
20 ፤ ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደ ሆነ ምን ላድርግልህ?ስለ ምን እኔን ለአንተ ዓላማ አደረግኸኝ?ስለ ምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ?
21 ፤ ስለ ምን መተላለፌን ይቅር አትልም?ኃጢአቴንስ ስለ ምን አታስወግድልኝም?አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፤ማለዳ ትፈልገኛለህ፥ አታገኘኝም።