መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 14

1 ፤ ከሴት የተወለደ ሰውየሕይወቱ ዘመን ጥቂት ቀን ነው፥ መከራም ይሞላዋል።
2 ፤ እንደ አበባ ይወጣል፥ ይረግፋልም፤እንደ ጥላም ይሸሻል፥ እርሱም አይጸናም።
3 ፤ እንደዚህስ ባለ ሰው ላይ ዓይኖችህን ትከፍታለህን?ከአንተስ ጋር እኔን ወደ ፍርድ ታገባለህን?
4 ፤ ከርኩስ ነገር ንጹሕን ሊያወጣ ማን ይችላል?አንድ እንኳ የሚችል የለም።
5 ፤ የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፥የወሩም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፥እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት።
6 ፤ እንደ ምንደኛ ዕድሜው እስኪፈጸም ድረስያርፍ ዘንድ ከእርሱ ጥቂት ዘወር በል።
7 ፤ ዛፍ ቢቈረጥ ደግሞ ያቈጠቍጥ ዘንድ፥ቅርንጫፉም እንዳያልቅ ተስፋ አለው።
8 ፤ ሥሩም በምድር ውስጥ ቢያረጅ፥ግንዱም በመሬት ውስጥ ቢሞት፥
9 ፤ ከውኃ ሽታ የተነሣ ያቈጠቍጣል፤እንደ አትክልት ቅርንጫፍ ያወጣል።
10 ፤ ሰው ግን ይሞትና ይጋደማል፤ሰውም ነፍሱን ይሰጣል፥ እርሱስ ወዴት አለ?
11 ፤ ውኃ ከባሕር ውስጥ ያልቃል፤ወንዙም ያንሳል ይደርቅማል።
12 ፤ ሰውም ተኝቶ አይነሣም፤ሰማይ እስኪያልፍ ድረስ አይነቃም፥ከእንቅልፉም አይነሣም።
13 ፤ በሲኦል ውስጥ ምነው በሰወርኸኝ ኖሮ!ቍጣህ እስኪያልፍ ድረስ በሸሸግኸኝ ኖሮ!ቀጠሮም አድርገህ ምነው ባሰብኸኝ ኖሮ!
14 ፤ በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን?መለወጤ እስኪመጣ ድረስ፥የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር።
15 ፤ በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር፤የእጅህንም ሥራ በተመኘኸው ነበር።
16 ፤ አሁን ግን እርምጃዬን ቈጥረኸዋል፤ኃጢአቴንም ትጠባበቃለህ።
17 ፤ መተላልፌ በከረጢት ውስጥ ታትሞአል፥ኃጢአቴንም ለብጠህበታል።
18 ፤ ተራራ ሲወድቅ ይጠፋል፥ዓለቱም ከስፍራው ይፈልሳል፤
19 ፤ ውኆች ድንጋዮቹን ይፍቃሉ፤ፈሳሾቹም የምድሩን አፈር ይወስዳሉ፤እንዲሁ የሰውን ተስፋ ታጠፋዋለህ።
20 ፤ ለዘላለም ታሸንፈዋለህ፥ እርሱም ያልፋል፤ፊቱን ትለውጣለህ፥ እርሱንም ትሰድደዋለህ።
21 ፤ ልጆቹ ቢከብሩ አያውቅም፤ቢዋረዱም አያይም።
22 ፤ ነገር ግን የገዛ ሥጋው ሕመም ብቻ ይሰማዋል፥ለራሱም ብቻ ያለቅሳል። ች