መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 4
1 ፤ ቴማናዊውም ኤልፋዝ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ አንድ ሰው ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ ቢሞክር ትቀየማለህን?ቃልንስ ከመናገር ሊቀር የሚችል ማን ነው?
3 ፤ እነሆ፥ አንተ ብዙዎችን ታስተምር ነበር፥የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፥
4 ፤ ቃልህ የሚሰናከለውን ያስነሣ ነበር፥አንተም የሚብረከረከውን ጕልበት ታጸና ነበር።
5 ፤ አሁን ግን በአንተ ላይ መጥቶአል፥ አንተም ደከምህ፤ደርሶብሃል፥ አንተም ተቸገርህ።
6 ፤ አምላክህን መፍራትህ መጽናናትህ፥የቅንነትህም መንገድ ተስፋህ አይደለምን?
7 ፤ እባክህ አስብ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው?ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማን ነው?
8 ፤ እኔ እንዳየሁ፥ ኃጢአትን የሚያርሱ፥መከራንም የሚዘሩ ይህንኑ ያጭዳሉ።
9 ፤ በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፥በቍጣውም መንፈስ ያልቃሉ።
10 ፤ የአንበሳ ጩኸት፥ የጩዋኺ አንበሳ ድምፅ፥የአንበሳ ደቦል ጥርስ ተሰባበረ።
11 ፤ አሮጌ አንበሳ አደን በማጣት ይሞታል፥የአንበሳይቱም ግልገሎች ይበተናሉ።
12 ፤ ለእኔም በምሥጢር ቃል መጣልኝ፥ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች።
13 ፤ በሌሊት ሕልም አሳብ ሲነሣ፥የከበደም እንቅልፍ በሰው ላይ ሲወድቅ፥
14 ፤ አጥንቴን ሁሉ ያናወጡድንጋጤና መንቀጥቀጥ ወደቁብኝ።
15 ፤ መንፈስም በፊቴ አለፈ፤የሥጋዬ ጠጕር ቆመ።
16 ፤ እርሱም ቆመ፥ መልኩን ግን ለመለየት አልቻልሁም፥ምሳሌም በዓይኔ ፊት ነበረ፤የዝምታ ድምፅ ሰማሁ።
17 ፤ በውኑ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ሊሆን፥ወይስ ሰው በፈጣሪው ፊት ሊነጻ ይችላልን?
18 ፤ እነሆ፥ በባሪያዎቹ አይታመንም፤መላእክቱንም ስንፍና ይከስሳቸዋል፤
19 ፤ ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ፥መሠረታቸው በትቢያ ውስጥ የሆነ፥ከብል በፊት የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ?
20 ፤ በጥዋትና በማታ መካከል ይሰባበራሉ፤ማንም ሳያስብ ለዘላለም ይጠፋሉ።
21 ፤ ገመዳቸው የተነቀለ አይደለምን?አለጥበብም ይሞታሉ።