መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 40
1 ፤ እግዚአብሔርም መለሰ ኢዮብንም እንዲህ አለው።
2 ፤ በውኑ የሚከራከር ሰው ሁሉን ከሚችል አምላክ ጋር ይከራከራልን?ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋቀስ እርሱ ይመልስለት።
3 ፤ ኢዮብም መለሰ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው።
4 ፤ እነሆ፥ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ፤ የምመልስልህ ምንድር ነው?እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ።
5 ፤ አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ አልመልስምም፤ሁለተኛ ጊዜም፥ ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም።
6 ፤ እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ።
7 ፤ እንግዲህ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።
8 ፤ በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን?አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ትፈርዳለህን?
9 ፤ እንደ እግዚአብሔር ክንድ ያለ ክንድ አለህን?ወይስ እንደ እርሱ ባለ ድምፅ ታንጐደጕዳለህን?
10 ፤ በታላቅነትና በልዕልና ተላበስ፤በክብርና በግርማም ተጐናጸፍ።
11 ፤ የቍጣህን ፈሳሽ አፍስስ፤ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልክተህ አዋርደው።
12 ፤ ትዕቢተኛውንም ሁሉ ተመልከት፥ ዝቅ ዝቅም አድርገው፤በደለኞችንም ወዲያውኑ እርገጣቸው።
13 ፤ በአፈር ውስጥ በአንድነት ሰውራቸው፤በተሸሸገም ስፍራ ፊታቸውን ሸፍን።
14 ፤ በዚያን ጊዜም ቀኝ እጅህ ታድንህ ዘንድ እንድትችልእኔ ደግሞ እመሰክርልሃለሁ።
15 ፤ ከአንተ ጋር የሠራሁትን ጉማሬ፥ እስኪ፥ ተመልከት፤እንደ በሬ ሣር ይበላል።
16 ፤ እነሆ፥ ብርታቱ በወገቡ ውስጥ ነው፤ኃይሉም በሆዱ ጅማት ውስጥ ነው።
17 ፤ ጅራቱን እንደ ጥድ ዛፍ ያወዛውዛል፤የወርቹ ጅማት የተጐነጐነ ነው።
18 ፤ አጥንቱ እንደ ናስ አገዳ ነው፤አካላቱ እንደ ብረት ዘንጎች ናቸው።
19 ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፍጥረት አውራ ነው፤ሠሪውም ሰይፉን ሰጠው።
20 ፤ የሜዳ እንስሶች ሁሉ የሚጫወቱበት ተራራምግብን ያበቅልለታል።
21 ፤ ጥላ ካለው ዛፍ በታች፥በደንገልና በረግረግ ውስጥ ይተኛል።
22 ፤ ጥላ ያለው ዛፍ በጥላው ይሰውረዋል፤የወንዝ አኻያ ዛፎች ይከብቡታል።
23 ፤ እነሆ፥ ወንዙ ቢጐርፍ አይደነግጥም፤ዮርዳኖስም እስከ አፉ ድረስ ቢፈስስ እርሱ ይተማመናል።
24 ፤ ዓይኖቹ እያዩ ይያዛልን?አፍንጫውስ በወጥመድ ይበሳልን?[25]፤ በውኑ አዞውን በመቃጥን ታወጣለህን?ምላሱንስ በገመድ ታስረዋለህን?[26]፤ ወይስ ስናጋ በአፍንጫው ታደርጋለህን?ወይስ በችንካር ጕንጩን ትበሳለህን?[27]፤ በውኑ ወደ አንተ እጅግ ይለምናልን?በጣፈጠስ ቃል ይናገርሃልን?[28]፤ በውኑ ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን ይገባልን?ወይስ ለዘላለም ባሪያ ታደርገዋለህን?[29]፤ ከወፍ ጋር እንደምትጫወት ከእርሱ ጋር ትጫወታለህን?ወይስ ለሴት ባሪያዎችህ ታስረዋለህን?[30]፤ አጥማጆች በእርሱ ይከራከራሉን?ወይስ ነጋዴዎች ያካፍሉታልን?[31]፤ በውኑ ቁርበቱን በጭሬ፥ራሱንስ በዓሣ ጦር ትሞላዋለህን?[32]፤ እጅህን በላዩ ጫን፤ሰልፉን አስብ፥ እንግዲህም አትድገም።