መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 5

1 ፤ አሁንም ጥራ፤ የሚመልስልህ አለን?ከቅዱሳንስ ወደማናቸው ትዞራለህ?
2 ፤ ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋል፥ሰነፉንም ቅንዓት ያጠፋዋል።
3 ፤ ሰነፍ ሰው ሥር ሰድዶ አየሁት፥ድንገትም መኖሪያውን ረገምሁ።
4 ፤ ልጆቹም ከደኅንነት ርቀዋል፥በበርም ውስጥ ተረግጠዋል፥የሚታደጋቸውም የለም።
5 ፤ የሰበሰበውንም ራብተኛ ይበላዋል፥ከእሾህም ውስጥ እንኳ ያወጣዋል፤የተጠማ ሀብታቸውን ዋጠ።
6 ፤ ችግር ከትቢያ አይመጣም፥መከራም ከመሬት አይበቅልም፤
7 ፤ የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥ሰው እንዲሁ ለመከራ ተወልዶአል።
8 ፤ እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምን ነበር፥ነገሬንም ወደ እግዚአብሔር አቀርብ ነበር።
9 ፤ የማይመረመረውን ታላቅ ነገርናየማይቈጠረውን ተአምራት ያደርጋል።
10 ፤ በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥በእርሻም ላይ ውኃ ይልካል።
11 ፤ የተዋረዱትን ወደ ላይ ያወጣል፥ኀዘንተኞችንም ለደኅንነት ከፍ ከፍ ያደርጋቸዋል።
12 ፤ እጃቸውም ምክራቸውን እንዳይፈጽምየተንኰለኞችን አሳብ ከንቱ ያደርገዋል።
13 ፤ ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤የጠማሞችንም ምክር ይዘረዝራል።
14 ፤ በቀን ጨለማን ያገኛሉ፥በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ።
15 ፤ ድሀውንም ከአፋቸው ሰይፍከኃያሉም እጅ ያድነዋል።
16 ፤ ለምስኪኑም ተስፋ አለው፤ክፋት ግን አፍዋን ትዘጋለች።
17 ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፤ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ።
18 ፤ እርሱ ይሰብራል፥ ይጠግንማል፤ያቈስላል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ።
19 ፤ በስድስት ክፉ ነገር ውስጥ ያድንሃል፥በሰባትም ውስጥ ክፋት አትነካህም።
20 ፤ በራብ ጊዜ ከሞት፥በሰልፍም ከሰይፍ እጅ ያድንሃል።
21 ፤ ከምላስ ጅራፍ ትሰወራለህ፤ጥፋትም ሲመጣ አትፈራም።
22 ፤ በጥፋትና በራብ ላይ ትስቃለህ፤ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፤
23 ፤ ቃል ኪዳንህ ከምድረ በዳ ድንጋይ ጋር ይሆናልና፤የምድረ በዳም አራዊት ከአንተ ጋር ይስማማሉና።
24 ፤ ድንኳንህም በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፤በረትህን ትጐበኛለህ አንዳችም አይጐድልብህም።
25 ፤ ዘርህም ታላቅ እንዲሆን፥ትውልድህም እንደ ምድር ሣር እንዲሆን ታውቃለህ።
26 ፤ በወራቱ የእህሉ ነዶ ወደ አውድማ እንዲገባ፥በረጅም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ።
27 ፤ እነሆ፥ ይህችን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፤አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ እወቀው።