መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 11
1 ፤ ነዕማታዊውም ሶፋር መለስ እንዲህም አለ።
2 ፤ በውኑ ለቃል ብዛት መልስ መስጠት አይገባምን?ወይስ ተናጋሪ ሰው እንደ ጻድቅ ይቈጠራልን?
3 ፤ ትምክህትህስ ሰዎችን ዝም ያሰኛቸዋልን?ብትሳለቅስ የሚያሳፍርህ የለምን?
4 ፤ አንተ። ትምህርቴ የተጣራ ነው፥በዓይንህም ፊት ንጹሕ ነኝ ትላለህ።
5 ፤ ምነው እግዚአብሔር ቢናገርህ!በአንተም ላይ ከንፈሩን ቢከፍት!
6 ፤ የጥበቡን ምሥጢር ቢገልጥልህ!ማስተዋሉ ብዙ ነውና።እግዚአብሔር ለበደልህ ከሚገባው አሳንሶ እንደሚያስከፍልህ እወቅ።
7 ፤ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምር ትችላለህን?ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክ ፈጽመህ ልትመረምር ትችላለህን?
8 ፤ ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ?ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ?
9 ፤ ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል።
10 ፤ እርሱ ቢያልፍ፥ ቢዘጋም፥ ጉባኤንም ቢሰበስብ፥የሚከለክለው ማን ነው?
11 ፤ ምናምንቴዎችን ሰዎች ያውቃልና፥በደልንም ሲያይ ዝም ብሎ አይመለከትም።
12 ፤ የሜዳ አህያ ግልገል ሰው ሆኖ ቢወለድ፥ያን ጊዜ ከንቱ ሰው ጥበብን ያገኛል።
14 ፤ በእጅህ በደል ቢኖር አርቀው፤በድንኳንህም ኃጢአት አይኑር፤አንተ ልብህን ቅን ብታደርግ፥እጅህንም ወደ እርሱ ብትዘረጋ፥
15 ፤ በዚያን ጊዜ በእውነት ፊትህን ያለ ነውር ታነሣለህ፤ትበረታለህ፥ አትፈራምም።
16 ፤ መከራህንም ትረሳለህ፤እንዳለፈ ውኃ ታስበዋለህ።
17 ፤ ከቅትር ይልቅ ሕይወትህ ይበራል፤ጨለማም ቢሆን እንደ ጥዋት ይሆናል።
18 ፤ ተስፋም ስላለህ ተዘልለህ ትቀመጣለህ፤በዙሪያህ ትመለከታለህ፥ በደኅንነትም ታርፋለህ።
19 ፤ ትተኛለህ፥ የሚያስፈራህም የለም፤ብዙ ሰዎችም ልመና ያቀርቡልሃል።
20 ፤ የክፉዎች ዓይን ግን ትጨልማለች፤የሚሸሹበትንም ያጣሉ፥ተስፋቸውም ነፍሳቸውን ማውጣት ነው።