መጽሐፈ ኢዮብ።. Chapter 18

1 ፤ ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ።
2 ፤ እስከ መቼ ቃልን ታጠምዳለህ?አስተውል፥ ከዚያም በኋላ እንናገራለን።
3 ፤ ስለ ምንስ እንደ እንስሶች ተቈጠርን?ስለ ምንስ በዓይንህ ፊት ረከስን?
4 ፤ ቍጣ ወርሶሃል፤ አንተስ የሞትህ እንደ ሆነ፥ምድር ስለ አንተ ባድማ ትሆናለችን?ወይስ ዓለት ከስፍራው ይነቀላልን?
5 ፤ የኃጢአተኛ መብራት ይጠፋል፥የእሳቱም ነበልባል ብልጭ አይልም።
6 ፤ ብርሃን በድንኳኑ ውስጥ ይጨልማል፥መብራቱም በላዩ ይጠፋል።
7 ፤ የኃይሉም እርምጃ ትጠብባለች፥ምክሩም ትጥለዋለች።
8 ፤ እግሩ በወጥመድ ትያዛለች፥በመረብም ላይ ይሄዳል።
9 ፤ አሽክላ ሰኰናውን ይይዛል፥ወስፈንጠርም ይበረታበታል።
10 ፤ በምድር ላይ የሸምቀቆ ገመድ፥በመንገዱም ላይ ወጥመድ ለእርሱ ተሰውራለች።
11 ፤ ድንጋጤ በዙሪያው ታስፈራዋለች፥በስተ ኋላውም ሆና ታባርራቸዋለች።
12 ፤ ኃይሉ በራብ ትደክማለች፥መቅሠፍትም እስኪሰናከል ተዘጋጅቶለታል።
13 ፤ የሰውነቱ ብልቶች ይጠፋሉ፤የሞትም በኵር ልጅ ብልቶቹን ይበላል።
14 ፤ ከሚታመንበት ድንኳን ይነቀላል፤ወደ ድንጋጤም ንጉሥ ያስቸኵሉታል።
15 ፤ በድንኳኑ ውስጥ ለእርሱ የማይሆነው ይኖራል፤በመኖሪያውም ላይ ዲን ይበተናል።
16 ፤ ሥሩ ከበታቹ ይደርቃል፥ጫፉም ከበላይ ይረግፋል።
17 ፤ መታሰቢያው ከምድር ላይ ይጠፋል፥በሜዳም ስም አይቀርለትም።
18 ፤ ከብርሃን ወደ ጨለማ ያፈልሱታል፥ከዓለምም ያሳድዱታል።
19 ፤ ዘርም ትውልድም በሕዝቡ መካከል አይሆንለትም፤በመኖሪያውም ውስጥ የሚቀመጥ ሰው አይቀርለትም።
20 ፤ የፊተኞች ሰዎች እንደ ደነገጡ፥እንዲሁ የኋለኞች ሰዎች ስለ ዘመኑ ይደነቃሉ።
21 ፤ በእውነት የኃጢአተኞች ቤት እንዲሁ ናት፥እግዚአብሔርንም የማያውቅ ሰው ስፍራ ይህ ነው።