ትንቢተ ኤርምያስ. Chapter 38

1 ኤርምያስም ለሕዝቡ ሁሉ የተናገረውን ቃል የማታን ልጅ ስፋጥያስ፥ የጳስኮርም ልጅ ጎዶልያስ፥ የሰሌምያም ልጅ ዮካል፥ የመልክያም ልጅ ጳስኮር ሰሙ።
2 ኤርምያስ እንዲህ ብሎአልና። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በዚህች ከተማ የሚቀመጥ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወደ ከለዳውያን ግን የሚወጣ በሕይወት ይኖራል፥ ነፍሱም እንደ ምርኮ ትሆንለታለች፥ በሕይወትም ይኖራል።
3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና። ይህች ከተማ በባቢሎን ንጉሥ ሠራዊት እጅ በእርግጥ ትሰጣለች፥ እርሱም ይይዛታል።
4 አለቆቹም ንጉሡን። ይህን የመሰለውን ቃል ሲነግራቸው በዚህች ከተማ የቀሩትን የሰልፈኞቹን እጅ የሕዝቡንም ሁሉ እጅ ያደክማልና ይህ ሰው እንዲገደል እንለምንሃለን፤ ይህ ሰው ክፋትን እንጂ ለዚህ ሕዝብ ሰላምን አይመኝለትምና አሉት።
5 ንጉሡም ሴዴቅያስ። ንጉሡ በእናንተ ላይ ምንም ሊያደርግ አይችልምና እነሆ፥ በእጃችሁ ነው አለ።
6 ኤርምያስንም ወሰዱት በግዞት ቤቱም አደባባይ ወደ ነበረው ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ መልክያ ጕድጓድ ውስጥ ጣሉት፤ ኤርምያስንም በገመድ አወረዱት። በጕድጓድም ውስጥ ጭቃ እንጂ ውኃ አልነበረበትም፤ ኤርምያስም ወደ ጭቃው ውስጥ ገባ።
7 በንጉሡም ቤት የነበረው ጃንደረባ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ኤርምያስን በጕድጓዱ ውስጥ እንዳኖሩት ሰማ። ንጉሡም በብንያም በር ተቀምጦ ነበር።
8 አቤሜሌክም ከንጉሡ ቤት ወጥቶ ንጉሡን እንዲህ አለው።
9 ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ነቢዮን ኤርምያስን በጕድጓድ ውስጥ በመጣላቸው በእርሱ ላይ በማድረጋቸው ሁሉ ክፉ አድርገዋል፤ በከተማይቱም ውስጥ እንጀራ ስለሌለ በዚያ በራብ ይሞታል።
10 ንጉሡም ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክም። ከአንተ ጋር ሠላሳ ሰዎች ከዚህ ውሰድ፥ ነቢዩም ኤርምያስ ሳይሞት ከጕድጓድ አውጣው ብሎ አዘዘው።
11 አቤሜሌክም ከእርሱ ጋር ሰዎችን ይዞ ሄደ፥ ከቤተ መዛግብቱም በታች ወደ ነበረው ወደ ንጉሥ ቤት ገባ፥ ከዚያም አሮጌ ጨርቅና እላቂ ልብስ ወሰደ፥ ወደ ኤርምያስም ወደ ጉድጓድ ውስጥ በገመድ አወረደው።
12 ኢትዮጵያዊውም አቤሜሌክ ኤርምያስን። ይህን አሮጌ ጨርቅና እላቂውን ልብስ በብብትህ ከገመዱ በታች አድርግ አለው፤ ኤርምያስም እንዲሁ አደረገ።
13 ኤርምያስንም በገመዱ ጐተቱት ከጕድጓድም አወጡት፥ ኤርምያስም በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ።
14 ንጉሡም ሴዴቅያስ ልኮ በእግዚአብሔር ቤት ወደ ነበረው ወደ ሦስተኛው መግቢያ ወደ እርሱ ነቢዩን ኤርምያስን አስመጣው፤ ንጉሡም ኤርምያስን። አንዲት ነገር እጠይቅሃለሁ፤ ምንም አትሸሽገኝ አለው።
15 ኤርምያስም ሴዴቅያስን። ብነግርህ በውኑ አትገድለኝምን? ብመክርህም አትሰማኝም አለው።
16 ንጉሡም ሴዴቅያስ። ይህችን ነፍስ የፈጠረልን ሕያው እግዚአብሔርን! አልገድልህም፥ ነፍስህንም ለሚሹ ለእነዚህ ሰዎች እጅ አሳልፌ አልሰጥህም ብሎ በቈይታ ለኤርምያስ ማለ።
17 ኤርምያስም ሴዴቅያስን። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ብትወጣ፥ ነፍስህ በሕይወት ትኖራለች ይህችም ከተማ በእሳት አትቃጠልም፤ አንተም ቤትህም በሕይወት ትኖራላችሁ።
18 ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ባትወጣ ግን፥ ይህች ከተማ በከለዳውያን እጅ ትሰጣለች፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል አንተም ከእጃቸው አታመልጥም አለው።
19 ንጉሡም ሴዴቅያስ ኤርምያስን። ወደ ከለዳውያን በኰበለሉት በአይሁድ እጅ አሳልፈው ይሰጡኛል እነርሱም ያፌዙብኛል ብዬ እፈራለሁ አለው።
20 ኤርምያስም እንዲህ አለው። አሳልፈው አይሰጡህም። እኔ የምነግርህን የእግዚአብሔርን ቃል እባክህ፥ ስማ፤ ይቀናሃል ነፍስህም በሕይወት ትኖራለች።
21 ትወጣ ዘንድ እንቢ ብትል ግን፥ እግዚአብሔር ያሳየኝ ቃል ይህ ነው።
22 እነሆ፥ በይሁዳ ንጉሥ ቤት የቀሩትን ሴቶች ሁሉ ወደ ባቢሎን ንጉሥ አለቆች ያወጣሉ፤ እነዚያም ሴቶች። ባለምዋሎችህ አታልለውሃል አሸንፈውህማል፤ እግሮችህ ግን አሁን በጭቃ ውስጥ ከገቡ እነርሱ ከአንተ ወደ ኋላ ተመልሰዋል ይላሉ።
23 ሚስቶችህንና ልጆችህንም ሁሉ ወደ ከለዳውያን ያወጣሉ፤ አንተም በባቢሎን ንጉሥ እጅ ትያዛለህ እንጂ ከእጃቸው አታመልጥም፤ ይህችም ከተማ በእሳት ትቃጠላለች።
24 ሴዴቅያስም ኤርምያስን እንዲህ አለው። ይህም ቃል ማንም አይወቅ፥ አንተም አትሞትም።
25 አለቆቹ ግን እኔ ከአንተ ጋር እንደ ተነጋገርሁ ቢሰሙ፥ ወደ አንተም መጥተው። ለንጉሡ ያልኸውን ንገረን አትሸሽገንም፥ እኛም አንገድልህም፤ ደግሞ ንጉሡ ያለህን ንገረን ቢሉህ፥ አንተ።
26 በዚያ እሞት ዘንድ ወደ ዮናታን ቤት አትመልሰኝ ብዬ በንጉሡ ፊት ለመንሁ በላቸው።
27 አለቆቹም ሁሉ ወደ ኤርምያስ መጥተው ጠየቁ፥ ንጉሡም እንዳዘዘው እንደዚህ ቃል ሁሉ ነገራቸው። ነገሩም አልተሰማምና ከእርሱ ጋር መነጋገርን ተው።
28 ኢየሩሳሌም እስከ ተያዘችበት ቀን ድረስ በግዞት ቤት አደባባይ ተቀመጠ።