ትንቢተ ኤርምያስ. Chapter 9
1 ተወግተው ስለ ሞቱ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ!
2 ሁሉም አመንዝሮች፥ የአታላዮች ጉባኤ ናቸውና ሕዝቤን እተዋቸው ዘንድ ከእነርሱም እለይ ዘንድ በምድረ በዳ የመንገደኞች ማደሪያን ማን በሰጠኝ?
3 ምላሳቸውን ስለ ሐሰት እንደ ቀስት ገተሩ፤ በምድር በረቱ ነገር ግን ለእውነት አይደለም፤ ከክፋት ወደ ክፋት ይሄዳሉና እኔንም አላወቁምና፥ ይላል እግዚአብሔር።
4 ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ ያማልና እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፥ በወንድሞቻችሁም አትታመኑ።
5 ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ያታልላል በእውነትም አይናገርም፤ ሐሰትን መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፥ ክፉንም ለማድረግ ይደክማሉ።
6 ማደሪያህ በሽንገላ መካከል ነው፥ ከሽንገላም የተነሣ እኔን ያውቁኝ ዘንድ እንቢ ብለዋል፥ ይላል እግዚአብሔር።
7 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ አቀልጣቸዋለሁ እፈትናቸውማለሁ፤ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ክፋት ከዚህ ሌላ የማደርገው ምንድር ነው?
8 ምላሳቸው የተሳለ ፍላጻ ነው፤ ሽንገላን ይናገራሉ ሰው ከባልንጀራው ጋር በሰላም ይናገራል፥ በልቡ ግን ያደባበታል።
9 በውኑ ስለዚህ ነገር አልቀሥፍምን? ይላል እግዚአብሔር፤ ነፍሴስ እንደዚህ ባለ ሕዝብ ላይ አትበቀልምን?
10 ለተራሮች ልቅሶን ለምድረ በዳ ማሰማርያዎችም ዋይታን አነሣለሁ፥ ሰው እንዳያልፍባቸው በእሳት ተቃጥለዋልና። ሰዎችም የከብቱን ድምፅ አይሰሙም፤ ከሰማይ ወፎች ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ሸሽተው ሄደዋል።
11 ኢየሩሳሌምንም የፍርስራሽ ክምር የቀበሮም ማደሪያ አደርጋታለሁ፥ የይሁዳንም ከተሞች ሰው የማይቀመጥባት ባድማ አደርጋቸዋለሁ።
12 ይህን የሚያስተውል ጠቢብ ሰው ማን ነው? ያወራስ ዘንድ የእግዚአብሔር አፍ ለማን ተናገረ? ሰው እንዳያልፍባት ምድርስ ስለምን ጠፋች፥ እንደ ምድረ በዳስ ስለ ምን ተቃጠለች?
13 እግዚአብሔርም እንዲህ አለ። የሰጠኋቸውን ሕጌን ትተዋልና፥ ቃሌንም አልሰሙምና፥
14 ነገር ግን የልባቸውን ምኞትና አባቶቻቸው ያስተማሩአቸውን በኣሊምን ተከትለዋልና
15 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ይህን ሕዝብ እሬትን አበላዋለሁ የሐሞትንም ውኃ አጠጣዋለሁ።
16 እነርሱና አባቶቻቸውም ባላወቁአቸው አሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፥ እስካጠፋቸውም ድረስ በስተ ኋላቸው ሰይፍን እሰድድባቸዋለሁ።
17 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንዲመጡ አልቃሾች ሴቶችን ጥሩ፤ እንዲመጡም ወደ ብልሃተኞች ሴቶች ላኩ፤
18 ዓይኖቻችንም እንባ እንዲያፈስሱ የዓይናችንም ሽፋሽፍቶች ውኃን እንዲያፈልቁ ፈጥነው ለእኛ ልቅሶውን ይያዙ።
19 በጽዮን። እንዴት ተበዘበዝን! ምድርንም ትተናልና፥ ቤቶቻችንንም አፍርሰዋልና እንዴት አፈርን! የሚል የልቅሶ ድምፅ ተሰምቶአል።
20 እናንተ ሴቶች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ ጆሮአችሁም የአፉን ቃል ትቀበል፥ ለሴቶች ልጆቻችሁም ልቅሶውን፥ እያንዳንዳችሁም ለባልንጀሮቻችሁ ዋይታውን አስተምሩ።
21 ሕፃናቱን ከመንገድ ጕልማሶቹንም ከአደባባይ ያጠፉ ዘንድ ሞት ወደ መስኮታችን ደርሶአል ወደ አዳራሻችንም ውስጥ ገብቶአል።
22 የሰውም ሬሳ እንደ ጕድፍ በእርሻ ላይ፥ ማንምም እንደማይሰበስበው ከአጫጆች በኋላ እንደሚቀር ቃርሚያ ይወድቃል።
23 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፥ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፥ ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤
24 ነገር ግን የሚመካው። ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፥ ይላል እግዚአብሔር።
26 አሕዛብ ሁሉ ያልተገረዙ ናቸውና፥ የእስራኤልም ቤት ሁሉ ልባቸው ያልተገረዘ ነውና የተገረዙትን ሁሉ፥ ግብጽንና ይሁዳን ኤዶምያስንም የአሞንንም ልጆች ሞዓብንም በምድረ በዳም የተቀመጡትን ጠጕራቸውን በዙሪያ የተላጩትን ሁሉ፥ ባለመገረዛቸው እነርሱን የምቀጣበት ዘመን እነሆ ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር።