ትንቢተ ኤርምያስ. Chapter 47

1 ፈርዖንም ጋዛን ሳይመታ ስለ ፍልስጥኤማውያን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ውኃ ከሰሜን ይነሣል የሚያጥለቀልቅም ፈሳሽ ይሆናል፤ በአገሪቱና በመላዋ ሁሉ፥ በከተማይቱና በሚኖሩባት ላይ ይጐርፋል፤ ሰዎቹም ይጮኻሉ፥ በምድርም የሚሮሩ ሁሉ ያለቅሳሉ።
3 ከኃይለኞች ፈረሶች ከኮቴያቸው መጠብጠብ ድምፅ፥ ከሰረገሎቹም መሸከርከር፥ ከመንኰራኵሮቹም መትመም የተነሣ አባቶች በእጃቸው ድካም ምክንያት ፊታቸውን መልሰው ወደ ልጆቻቸው አይመለከቱም።
4 ይህም የሚሆነው ፍልስጥኤማውያንን ሁሉ ያጠፋ ዘንድ የቀሩትንም ረዳቶች ሁሉ ከጢሮስና ከሲዶና ይቈርጥ ዘንድ ስለሚመጣው ቀን ነው፤ እግዚአብሔር ፍልስጥኤማውያንና የከፍቶርን ደሴት ቅሬታ ያጠፋልና።
5 ቡሀነት በጋዛ ላይ መጥቶአል፤ አስቀሎና ጠፋች፤ የዔናቅ ቅሬታዎች ሆይ! እስከ መቼ ድረስ ገላችሁን ትነጫላችሁ?
6 አንተ የእግዚአብሔር ሰይፍ ሆይ፥ ዝም የማትለው እስከ መቼ ነው? ወደ ሰገባህ ግባ ጸጥ ብለህም ዕረፍ።
7 እግዚአብሔር በአስቀሎናና በባሕር ዳር ላይ ትእዛዝ ሰጥቶአልና፥ በዚያም አዘጋጅቶታልና እንዴት ዝም ትላለህ?