ትንቢተ ሆሴዕ. Chapter 1
1 ፤ በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስም ዘመን በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2 ፤ እግዚአብሔር መጀመሪያ በሆሴዕ በተናገረ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሆሴዕን። ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ርቃ ታላቅ ግልሙትና ታደርጋለችና ሂድ፤ ጋለሞታን ሴትና የግልሙትናን ልጆች ለአንተ ውሰድ አለው።
3 ፤ እርሱም ሄዶ የዴቤላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደችለት።
4 ፤ እግዚአብሔርም። ከጥቂት ዘመን በኋላ የኢይዝራኤልን ደም በኢዩ ቤት ላይ እበቀላለሁና፥ ከእስራኤልም ቤት መንግሥትን እሽራለሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፤
5 ፤ በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ አለው።
6 ፤ ደግሞ ፀነሰች ሴት ልጅንም ወለደች። እግዚአብሔርም። ይቅር እላቸው ዘንድ የእስራኤልን ቤት ከእንግዲህ ወዲህ አልምርምና ስምዋን ሎሩሃማ ብለህ ጥራት፤
7 ፤ ነገር ግን የይሁዳን ቤት እምራለሁ፤ በአምላካቸውም በእግዚአብሔር አድናቸዋለሁ እንጂ በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በሰልፍ ወይም በፈረሶች ወይም በፈረሰኞች አላድናቸውም አለው።
8 ፤ ሎሩሃማም ጡት ባስጣለች ጊዜ፥ ደግሞ ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች።
9 ፤ እግዚአብሔርም። ሕዝቤ አይደላችሁምና፥ እኔም አምላክ አልሆናችሁምና ስሙን ሎዓሚ ብለህ ጥራው አለው።