ትንቢተ ሆሴዕ. Chapter 5

1 ፤ ካህናት ሆይ፥ ይህን ስሙ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ አድምጡ፤ የንጉሥ ቤት ሆይ፥ ልብ አድርጉ፤ በምጽጳ ላይ ወጥመድ፥ በታቦርም ላይ የተዘረጋ አሽክላ ሆናችኋልና ፍርድ በእናንተ ላይ ነው።
2 ፤ ዓመፀኞችም እርድ አብዝተዋል፤ እኔ ግን እነዚያን ሁሉ እዘልፋለሁ።
3 ፤ ኤፍሬምን አውቀዋለሁ፥ እስራኤልም ከእኔ አልተሰወረም፤ ኤፍሬም ሆይ፥ ዛሬ አመንዝረሃል፥ እስራኤልም ረክሶአል።
4 ፤ ወደ አምላካቸው ይመለሱ ዘንድ ሥራቸውን አላቀኑም፤ የግልሙትና መንፈስ በውስጣቸው አለና፤ እግዚአብሔርንም አላውቁምና።
5 ፤ የእስራኤልም ትዕቢት በፊቱ ይመሰክራል፤ ስለዚህ እስራኤልና ኤፍሬም በኃጢአታቸው ይሰናከላሉ፤ ይሁዳም ደግሞ ከእነሱ ጋር ይሰናከላል።
6 ፤ እግዚአብሔርንም ለመሻት በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ነድተው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱም ተመልሶአልና አያገኙትም።
7 ፤ ዲቃሎችን ልጆች ወልደዋልና እግዚአብሔርን ወንጅለዋል፤ አሁንም አንድ ወር እነርሱንና ርስታቸውን ይበላቸዋል።
8 ፤ በጊብዓ መለከትን፥ በራማ እንቢልታን ንፉና። ብንያም ሆይ፥ ከአንተ በኋላ እያላችሁ በቤትአዌን ላይ እሪ በሉ።
9 ፤ ኤፍሬም በዘለፋ ቀን የፈረሰ ይሆናል። በእስራኤል ነገዶች ዘንድ በእርግጥ የሚሆነውን ነገር ገልጫለሁ።
10 ፤ የይሁዳ አለቆች ድምበርን እንደሚነቅሉ ሆነዋል፤ እኔም መዓቴን እንደ ውኃ አፈስስባቸዋለሁ።
11 ፤ ኤፍሬም ከትእዛዝ በኋላ መሄድን ወድዶአልና የተገፋና በፍርድ የተጐዳ ሆኖአል።
12 ፤ እኔም ለኤፍሬም እንደ ብል፥ ለይሁዳም ቤት እንደ ነቀዝ ሆኜአለሁ።
13 ፤ ኤፍሬምም ደዌውን፥ ይሁዳም ቍስሉን ባየ ጊዜ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ ወደ ንጉሡም ወደ ኢያሪም መልእክተኛን ላከ፤ እርሱ ግን ይፈውሳችሁ ዘንድ፥ ከቊስላችሁም ያድናችሁ ዘንድ አልቻለም።
14 ፤ እኔም ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፥ ለይሁዳም ቤት እንደ አንበሳ ደቦል እሆናለሁና፤ እኔም ነጥቄ እሄዳለሁ እወስድማለሁ፥ የሚያድንም አይገኝም።
15 ፤ በደላቸውንም እስኪያውቁ ድረስ፥ ፊቴንም እስኪሹ ድረስ ሄጄ ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ፤ በመከራቸው ጊዜ እጅግ አድርገው ፊቴን ይፈልጋሉ።