ወደ ዕብራውያን. Chapter 12
1 -2 እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፥ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፥ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።
3 በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።
4 ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም፤
5 -6 እንደ ልጆችም ከእናንተ ጋር። ልጄ ሆይ፥ የጌታን ቅጣት አታቅልል፥ በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም፤ ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና፥ የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታችኋል።
7 ለመቀጣት ታገሡ፤ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርግላችኋልና፤ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?
8 ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኖአልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃላዎች እንጂ ልጆች አይደላችሁም።
9 ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋችን አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር፤ እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይወት ልንኖር በተገባን?
10 እነርሱ መልካም ሆኖ እንደ ታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና፥ እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል።
11 ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።
12 ስለዚህ የላሉትን እጆች የሰለሉትንም ጉልበቶች አቅኑ፤
13 ያነከሰውም እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ፥ ለእግራችሁ ቅን መንገድ አድርጉ።
14 ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፥ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና።
15 የእግዚአብሔር ጸጋ ለማንም እንዳይጎድለው፥ ብዙዎቹም የሚረክሱበት አንድ መራራ ሥር ወደ ላይ በቅሎ እንዳያስጨንቅ፥ ሴሰኛም የሚሆን እንዳይገኝ፥
16 ወይም ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚህ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይሆን ተጠንቀቁ።
17 ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደ ተጣለ ታውቃላችሁና፤ በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና።
18 ሊዳሰስ ወደሚችል ወደሚቃጠልም እሳት ወደ ጭጋግም ወደ ጨለማም ወደ ዐውሎ ነፋስም ወደ መለከት ድምፅም ወደ ቃሎችም ነገር አልደረሳችሁምና፤
19 ያንም ነገር የሰሙት ሌላ ቃል እንዳይጨመርባቸው ለመኑ፤
20 እንስሳ እንኳ ተራራውን ቢነካ ተወግሮ ይሙት የምትለውን ትእዛዝ ሊታገሡ አልቻሉምና፤
21 ሙሴም። እጅግ እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር፤
22 ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥
23 በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥
24 የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል።
25 ለሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ እነዚያ በምድር ላስረዳቸው እምቢ ባሉ ጊዜ ካላመለጡ፥ ከሰማይ ከመጣው ፈቀቅ የምንል እኛስ እንዴት እናመልጣለን?
26 በዚያም ጊዜ ድምፁ ምድርን አናወጠ፥ አሁን ግን። አንድ ጊዜ ደግሜ እኔ ሰማይን አናውጣለሁ እንጂ ምድርን ብቻ አይደለም ብሎ ተስፋ ሰጥቶአል።
27 ዳሩ ግን። አንድ ጊዜ ደግሜ የሚል ቃል፥ የማይናወጡት ጸንተው እንዲኖሩ፥ የሚናወጡት የተፈጠሩ እንደሚሆኑ ይለወጡ ዘንድ ያሳያል።
28 ስለዚህ የማይናወጥን መንግሥት ስለምንቀበል በማክበርና በፍርሃት እግዚአብሔርን ደስ እያሰኘን የምናመልክበትን ጸጋ እንያዝ፤
29 አምላካችን በእውነት የሚያጠፋ እሳት ነውና።