ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 28
1 ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ጠራው፥ ባረከውም፥ እንዲህ ብሎም አዘዘው። ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ፤
2 ፤ ተነሣና ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሂድ፤ ከዚያም ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች ሚስትን አግባ።
3 ፤ ሁሉን የሚችል አምላክም ለብዙ ሕዝብ ጉባኤ እንድትሆን ይባርክህ፥ ያፍራህ፥ ያብዛህ፤
4 ፤ ስደተኛ ሆነህ የተቀመጥህባትን እግዚአብሔርም ለአብርሃም የሰጣትን ምድር ትወርስ ዘንድ የአብርሃምን በርከት ለአንተ ይስጥህ፥ ለዘርህም እንዲሁ እንደ አንተ።
5 ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ሰደደው፥ እርሱም የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም የሚሆን የሶርያዊ ባቱኤል ልጅ ላባ ወዳለበት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሄደ።
6 ፤ ዔሳውም ይስሐቅ ያዕቆብን እንደ ባረከው ባየ ጊዜ፥ ከዚያም ሚስትን ያገባ ዘንድ ወደ ሁለት ወንዞች መካካል እንደ ሰደደው፥ በባረከውም ጊዜ። ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ ብሎ እንዳዘዘው፥
7 ፤ ያዕቆብም የአባቱንና የእናቱን ቃል ሰምቶ ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል እንደሄደ፥
8 ፤ የከነዓናውያንም ሴቶች ልጆች በአባቱ በይስሐቅ ፊት የተጠሉ እንደሆኑ ዔሳው ባየ ጊዜ፥
9 ፤ ዔሳው ወደ እስማኤል ሄደ፥ ማዕሌትንም በፊት ካሉት ሚስቶቹ ጋር ሚስት ትሆነው ዘንድ አገባ፤ እርስዋም የአብርሃም ልጅ የሆነ የእስማኤል ልጅና የነባዮት እኅት ናት።
10 ፤ ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ።
11 ፤ ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፥ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ፤ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሣ፥ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ።
12 ፤ ሕልምም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር።
13 ፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ። የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤
14 ፤ ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ።
15 ፤ እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።
16 ፤ ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ። በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፤ እኔ አላወቅሁም ነበር አለ።
17 ፤ ፈራ፥ እንዲህም አለ። ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።
18 ፤ ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፥ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፥ በላዩም ዘይትን አፈሰሰበት።
19 ፤ ያዕቆብም ያንን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፤ አስቀድሞ ግን የዚያች ከተማ ስም ሎዛ ነበረ።
20 ፤ ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን፥ በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ፥
21 ፤ ወደ አባቴ ቤትም በጤና ብመለስ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፤
22 ፤ ለሐውልት የተከልሁት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፤ ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ። a